ቀጥታ፡

ሮበርት ኦዶንካራ ከፈረሰኞቹ ጋር ተለያየ

አዲስ አበባ ጥቅምት 7/2011 ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር ተለያየ። ግብ ጠባቂው ከሰባት ዓመት ተኩል ቆይታ በኋላ ትናንት ከክለቡ ጋር መለያየቱን የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር አስታውቋል። ሮበርት ኦዶንካራ በ2003 ዓ.ም ፈረሰኞቹን ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ የነበረውን የሰባት ዓመት ተኩል ቆይታ ከሰበታ ከነማ ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሰለፍ መጀመሩ ይታወቃል። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለሃያ አንድ ተከታታይ ጨዋታዎች ግቡን ሳያስደፍር በመቆየት ባለክብረ ወሰን ከመሆኑ በተጨማሪ ከ2004 ዓ.ም እስከ 2008 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ዓመታት የኮከብ ግብ ጠባቂ ሽልማት ክብርን ለማሳካት መቻሉም ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በ2009 ዓ.ም በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ለተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርበት መቆየቱ የዛማሊክ ግብ ጠባቂ በሆነው አብዱልዋሃድ አል ሰይድ ተይዞ የቆየውን አህጉር አቀፍ ክብረ ወሰንንም መጋራት ችሏል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር 5 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፣ 2 የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ፣ 2 የአሸናፊዎች አሸናፊ፣ 4 የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ፣ በአጠቃላይ 13 ዋንጫዎችን በአሸናፊነት ማንሳቱም ይታወቃል። ክለቡ ከሮበርት ኦዶንካራ ጋር እግር ኳሳዊ በሆነ ምክንያት ቢለያይም ለቀጣይ የእግር ኳስ ህይወቱ ስኬትን እየተመኘ በክለቡ በነበረበት ወቅት ለሰጠው አገልግሎትና ለነበረው ቆይታ ማህበሩ ምስጋናውን አቅርቧል። ሮበርት ኦዶንካራ ከፈረሰኞቹ ከተለየ በኋላ ወደ አዳማ ከተማ መሄዱ እየተነገረ ነው። በዚህም በሁነኛ በረኛ እጦት ለሚቸገረው አዳማ ከተማ እንደሚጠቅም ተነግሯል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም