ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ስሎቫኒያ የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት ለመጀመር ተስማሙ

አዲስ አበባ ጥቅምት 7/2011 ኢትዮጵያና ስሎቫኒያ የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት ለመጀመር ተስማሙ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙትን የስሎቫኒያ ፕሬዚዳንት ቦሩት ፓሆር ዛሬ በምክር ቤት አነጋግረዋል። ምክትል አፈ ጉባኤዋ የኢትዮጵያ ፓርላማ የሚሰራቸውን ተግባራትና በውስጡ ያሉትን አደረጃጀቶች ለስሎቫኒያው ፕሬዝዳንትና ለልዕኡካን ቡድኑ ገለጻ አድርገውላቸዋል። የኢትዮጵያ ፓርላማ ህግ በማውጣትና አስፈጻሚውን አካል በመቆጣጠር ሰፊ ስራዎችን እንደሚሰራም እንዲሁ። ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን በተመለከተም የወጡ ፖሊሲዎች ሲተገበሩም ሆነ ማሻሻያ ሲደረግ የምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ክትትል እንደሚያደርግ ገልጸውላቸዋል። ፓርላማው መንግስትን በመደገፍና የወጡ ህጎችና መመሪያዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን በመገምገም ተጠያቂነትን ለማስፈን እየሰራ እንደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል። የሁለቱ አገሮች ፓርላማ አብረው ቢሰሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዝም ገልጸው ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ፓርላማ ጋር አብራ መስራት በሚያስችላት አካሄድ መሰረት ከስሎቫኒያ ጋርም ትሰራለች ብለዋል። በኢትዮጵያና የአውሮፓ ፓርላማ የወዳጅነት ኮሚቴ ውስጥ በአሰራሩ መሰረት ስሎቫኒያ ለማካተት እንደሚሰራም ተገልጾላቸዋል። የስሎቫኒያ ፕሬዚዳንት ቦሩት ፓሆር በበኩላቸው የስሎቫኒያ ፓርላማ አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን እንደሚሰጥ በመግለጽ ሌሎች ፓርላማው የሚሰራቸውን ተግባራትም አብራርተዋል። በቀጣይም የሁለቱ አገሮች ፓርላማ አብረው መስራት የሚያስችላቸው ጉዳዮችን በመለየት እንደሚሰሩም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። ስሎቫኒያ በልማት፣ በቱሪዝም፣ በንግድና ሌሎች ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጋር አብራ መስራት እንደምትፈልግም ገልጸዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላምን ለማስፈን እያደረገች ያለው ጥረት በተለይም በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር የተፈጠረውን ሰላም በማንሳት ለፕሬዝዳንቱ ተገልጾላቸዋል። ስሎቫኒያ በማር ምርት የታወቀች አገር በመሆኗም ልምዷን እንድታካፍልም ምክትል አፈ ጉባኤ ሽታዬ ጠይቀዋል። በተጨማሪም ሁለቱ አገራት አብረው መስራት በሚችሉባቸው በግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በልማትና ሰላም እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይም ተመካክረዋል። የኢትዮጵያና ስሎቫኒያ የኢኮኖሚ ግንኙነት ከ2 ሚሊዮን ዶላር በታች መሆኑም በምክክሩ ወቅት የተገለጸ ሲሆን ይህንን ለማሳደግ እንደሚሰራም ተስማምተዋል። በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የስሎቫኒያ ፕሬዚዳንት ቦሩት ፓሆር ዛሬ ጉብኝታቸውን እንደሚያጠናቅቁ ይጠበቃል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም