የሴት ካቢኔ አባላቱ ሹመት ለፖለቲካ አመራርነት ተሳትፎ መሰረት ይጥላል - ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ

አዲስ አበባ ጥቅምት 7/2011 የኢትዮጵያ መንግስት ከካቢኔ አባላቱ ግማሹን ሴቶችን ማድረጉ በከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ አመራርነት ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየተደረገ ላለው ጥረት መሰረት የሚጥል መሆኑን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ገለጹ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የቀረቡትን 20 የካቢኔ አባላት ሹመት ያጸደቀ ሲሆን አስሩ ሴቶች ናቸው። መንግስት ከካቢኔ አባላቱ ግማሹን ሴቶችን ማድረጉ የሴቶችን አቅም በማጎልበት  የፖለቲካ አመራርነት ተሳትፎ አቸውን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት መሰረት የሚጥል ነው ብለውታል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ 10 ሴቶች የካቢኔ አባላት እንዲሆኑ በመምረጣቸው ያላቸውን አድናቆት ገልጸው በአፍሪካ አህጉር ተመሳሳይ እርምጃ ይኖራል ብለው እንደሚጠብቁ መናገራቸውን ህብረቱ በድረ ገጹ አስፍሯል። ሊቀመንበሩ ኢትዮጵያ በሰብአዊና በሴቶች መብቶች ላይ የሚያተኩረው የማፑቶ ድንጋጌ ተግባራዊ እንዲሆን በፖርላማ ማጽደቋንም አድንቀዋል። ድንጋጌው ከ15 ዓመት በፊት የጸደቀና የሴቶችን መብት ለማስከበር ከወጡ ህጋዊ ሰነዶች በጣም ጠንካራና ከጊዜው ጋር የሚሄድ እንደሆነም አውስተዋል። የሴቶች እኩልነትና አቅም ማጎልበት ጽንሰ ሀሳብ በሁሉም የአፍሪካ ህብረት ሰነዶች እንደ ዋንኛ አጀንዳ ተደርጎ እንደተካተተም ነው ሙሳ ፋቂ ያስረዱት። በተለይም የአፍሪካ ህብረት የሚተዳደርበት ደንብ የሴቶች መብት እንዲከበር ትኩረት የሚሰጥ መሆኑንና ደንቡ ከህብረቱ ኮሚሽን የአመራርነት ቦታዎች በግማሹ ሴቶች እንዲሆኑ ከተቀመጠው ሀሳብ ጋር የሚሄድ እንደሆነም ጠቁመዋል። የአፍሪካ አገራት መሪዎች በሰኔ 2010 ዓ.ም በሞሪታኒያ ባካሄዱት ጉባኤ በጾታ እኩልነት እንዲሁም በሴቶች መብትና አቅም ማጎልበት የወሳኗቸውን ውሳኔዎች ሙሉ ለሙሉና በፍጥነት እንዲተገበሩ ለማድረግ ያላሳለሰ ጥረት እንደሚያደርግም አመልክተዋል። በሞሪታኒያው ጉባኤ መሪዎቹ ያሳለፉት ውሳኔ እ.አ.አ በ2025 በሁሉም የአፍሪካ ህብረት ተቋማትና የስራ ክፍሎች እኩል የጾታ ስብጥር እንዲኖር የሚያደርግና ህብረቱ እያካሄደ ያለው ተቋማዊ ለውጥ አካል እንደሆነም ነው ሙሳ ፋቂ ያስረዱት። በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሚስ ቬራ ሶንግዌ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በአፍሪካ 50 በመቶ የሴት ሚኒስትሮች ያሏት የመጀመሪያዋ አገር ኢትዮጵያ በመሆኗ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። በተመሳሳይ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለተመረጡት አዲስ ሴት ሚኒስትሮችም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። "አንድ ሀሳብ ተግባራዊ እስኪደረግ ያን ሀሳብ ፈጽሞ ማድረግ አይቻልም" የሚል አመለካከት እንዳለና በዚህ ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ውሳኔ ሊደነቅ እንደሚገባውም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የአየርላንድ ኤምባሲም በትዊተር ገጹ ባሰፈረው መልዕክት የአየርላንድ መንግስት ውሳኔውን ማድነቁንና በቀጣይ ከአዲሱ ካቢኔ ጋር መስራት እንደሚፈልግ አስታውቋል። ካቢኔው የለውጥ ሂደቱን የሚያስቀጥልና ለኢትዮጵያ ህዝብ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ይሰራል ብሎ እንደሚጠብቅም ኤምባሲው ገልጿል። ካቢኔው አዲስ ተሰጥኦ፣ ፍትሐዊ የጾታና የክልል ተዋጽኦ የሚታይበት እንደሆነና ይህም ሊደነቅ እንደሚገባው በትዊተር ገጹ የሰፈረው መረጃ ያመለክታል። የአየርላንድ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር በጤና፣ በማህበራዊ ጥበቃና በገጠር ልማት ዙሪያ በትብብር በመስራቱ ኩራት እንደሚሰማውም ነው ያተተው።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም