ዩንየኑ በ55 ሚሊዮን ብር የፓስታና ማካሮኒ ፋብሪካ ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩንየኑ በ55 ሚሊዮን ብር የፓስታና ማካሮኒ ፋብሪካ ሊገነባ ነው
አዳማ ጥቅምት 7/2011 የሉሜ አዳማ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩንየን በ55 ሚሊዮን ብር የፓስታና ማካሮኒ ፋብሪካ ግንባታ ለመጀመር ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ። የዩንየኑ ሥራ አስካይጅ አቶ ታደለ አብዲ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩንየኑ ግንባታውን የሚያካሂደው የገቢ ምንጩን በማስፋፋት የአባላቱን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ነው። "የፋብሪካውን ግንባታ ለማስጀመር ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ በሂደት ላይ ነው " ብለዋል ። ዩንየኑ ከዚህ ቀደም ባቋቋመው የዱቄት ፋብሪካን አማካኝነት ከአባል አርሶ አደሮች የሚሰበሰበውን ጥሬ የግብርና ምርት እሴት በመጨመር ለገበያ እያቀረበ ነው። በተጨማሪም የዳቦ ፋብሪካ አቋቁሞ በቀን 1ሺህ ዳቦ በማምረት ለህብረተሰቡና ለድርጅቶች እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል ። በተጠናቀቀው በጀት አመት ያመረተውን ዱቄት ለአካባቢው ህብረተሰብና ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አቅርቦ ከ10 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን ስራ አስኪያጁ አስታውሰዋል ። "እያደገ የመጣውን የአርሶ አደሩ ምርት በእሴት ሰንሰለት ውስጥ እንዲያልፍና የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ በማሰብ ዩንየኑ ሀብቱን ለግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንቨስትመንት እያዋለ ነው" ብለዋል ። ቦሶት፣ፈንታሌ፣ሉሜና አዳማ ወረዳዎች አባል አርሶ አደሮች ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑ የዋና ዋና ሰብሎችን በጥራትና በብዛት እንዲያመርቱ እየተደረገ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል ። በሎሜ ወረዳ የሸራ ዲባንዲባ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ወርቁ ደምሴ በበኩላቸው "ዩንየኑ ለምናመርተው ምርት ግብአት ከማቅረብ ጀምሮ ምርታችንን በተሻለ ዋጋ በመረከብ ተጠቃሚ እያደረገን ነው" ብለዋል ። የቦሰት ወረዳ ጠቅላላ ግብርና መሰረታዊ ማህበራት አባል አርሶ አደር ከድር ሃጂ ዩንየኑ ላቋቋመው የዳቦ ፋብሪካ የስንዴ ምርት እያቀረቡ መሆናቸውን ገልፀዋል ። "ዩንየኑ የፓስታና ማካሮኒ ፋብሪካ ለመገንባት መነሳሳቱም አባላቱን የበለጠ ተጠቃሚ ያደርገናል " ብለዋል ።