ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚነሱ ሃሳቦች ሃገራዊ ጥቅምን መሠረት ሊያደርጉ ይገባል... የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚነሱ ሃሳቦች ሃገራዊ ጥቅምን መሠረት ሊያደርጉ ይገባል... የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች
አሶሳ ጥቅምት 7/2011 ህዝብና ሃገርን በሚወክለው ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚነሱ ሀሳቦች ዘላቂና ብሔራዊ ጥቅምን መሠረት ማድረግ እንዳለባቸው አንዳንድ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ለሀገራዊ ለውጡ እንቅፋት እንዳይሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ገልጸዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ የሺዋስ እጅጉ እንዳሉት ሰንደቅ ዓላማ አገርና መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚወክል ምልክት በመሆኑ በዚህ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች አገራዊ ጥቅምን መሠረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡ " በሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚነሱ የሀሰብ ልዩነቶች በምንም መልኩ ለግጭት መንስኤ ሊሆኑ አይችሉም " ያሉት አስተያየት ሰጪው የጋራ መተማመን ከሌለ በውይይት ተነጋግሮ ማሻሻል ይቻላል ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ ህዝቡ ትክክለኛ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ መንግስት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የመስራት ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ ምልክቶችና አንዳንድ አርማዎች ከሰንደቅ ዓላማ ባልተናነሰ ትኩረት እያገኙ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በመሆኑም በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማና በአርማው ላይ የሚስተዋለው የአመላካከትና የአስተሳሰብ ብዥታዎች እንዲጠሩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። " ከሀገር አልፎ ለመላው ጥቁር ህዝቦች መመኪያና መኩሪያ የሆነው ሰንደቅ ዓላማ ሃገርንና ህዝብን የሚወክል እንጂ እርስ በርስ የመለያያ አጀንዳ መሆን አይገባውም " ሲሉም ገልጸዋል፡፡ መንግስት በየደረጃው የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት ፈጣን ውሳኔ ሊያሰጥበት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ አቶ ፍስሃ አያና የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው " ሕብረተሰቡ በሰንደቅ ዓላማ መነሻነት ወደአልተገባ ድርጊት ከመግባቱ በፊት በተለይ የአርማውን ትርጓሜና የመነሻ ታሪክ ጠንቀቆ ሊያውቅ ይገባል" ብለዋል፡፡ በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ የሚሰጡ ውሳኔዎች የመንግስት ወይም የመሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፍላጎት በማሰብ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ሃገራዊ ጥቅምን መሰረት ሊያደርጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ በሰነደቅ ዓላማው ላይ የተቀመጠው ዓርማ ህብረተሰቡ በሚገባ ተገንዝቦት እንዲያምነበት ለማድረግም በየደረጃው መድረክ አዘጋጅቶ ማወያየት እንደሚገባ ገልጸዋል። ''በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ህዝቡ ተቀራራቢ እምነት እንዲኖረው ቢደረግ አሁን ያለውን ሀገራዊ ለውጥ ይፋጥናል ብዬ አምናለሁ።'' ያለው ደግሞ ወጣት ኃይሉ አየሩ ነው። አሁን ካለው ሃገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር አንገብጋቢው ጉዳይ ሰንደቅ ዓላማ ሳይሆን ሀገራዊ ሠላምን በዘላቂነት ማስጠበቅ መሆን እንዳለበትም ወጣቱ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ብሔራዊ ኩራት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ናቸው ፡፡ ሰንደቅ ዓላማን ቀለል አድርገው የሚመለከቱ ወገኖች ቢኖሩም ጉዳዩ ከሃገራዊ እና ከብሔር ብረሰቦች ማንነት ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንዳለው ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ሃገራዊ ሰንደቅ ዓላማ ላይ አልፎ አልፎ የሚታዩ ክርክሮችና የሃሳብ ልዩነቶችን በሰለጠነ አግባብ መፍታት ይገባል ሲሉም አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታውቀዋል፡፡ በሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚነሱ የልዩነት ሃሳቦች ለሃገራዊ ለውጡ እንቅፋት እንዳይሆኑና በሠላማዊ መንገድ እንዲንጸባረቁ በመንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡