የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ41 ዓመታት በኋላ ወደ ሞቃዲሾ በረራ ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ41 ዓመታት በኋላ ወደ ሞቃዲሾ በረራ ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ ጥቅምት 7/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ ወደ ሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ በረራ ሊጀምር ነው። አየር መንገዱ በረራውን የሚጀምረው ከጥቅምት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚሆን ለኢዜአ ገልጿል። የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም የኢትዮጵያና የሶማሊያ መንግስታት ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ አየር መንገዱ ወደ ሞቃዲሾ ዳግም በረራውን እንዲጀመር ማድረጋቸውን ገልጸዋል። የበረራው መጀመር የሁለቱን ጎረቤትና እህትማማች አገሮች የህዝብ ለህዝብና የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በረራው በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ የሚኖሩ የሶማሊያ ዳያስፖራዎች በአዲስ አበባ አድርገው ወደ አገራችው እንዲጓዙም ያስችላል። የሚጀመረው በረራ በፍጥነት ወደ ዕለት ተዕለት በረራ እንደሚያድግ የገለጹት አቶ ተወልደ ይህም በሁለቱ አገራት፣ በሶማሊያና በተቀረው ዓለም መካከል ከፍተኛ የአየር ትራፊክ መጠን በመኖሩ እንደሆነ ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.አ.አ በ1970ዎቹ ወደ ሶማሊያ ያደርገው የነበረውን በረራ ካቋረጠ 41 ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በኋላ በድጋሚ ይጀምራል።