ኢቦላን የመከላከሉ አቅም የተሻለ ደረጃ ላይ ነው - ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2010 የኢቦላ ቫይረስን የመከላከል አቅም በተሻለ መልኩ መገንባቱን የዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገለጹ። ለአምስት ቀናት የሚቆየው የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት 71ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከተማ ተጀምሯል። ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ቴድሮስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ዳግም ያገረሸውን የኢቦላ ቫይረስ ለመከላከልና ለማስቆም የጤና ድርጅቱና ሌሎች የህክምና ባለሙያዎች ያለመታከት እየሰሩ ነው። ባለፈው ሳምንት ከሥራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን ዴሞክራቲክ ኮንጎ በማቅናት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት መመልከታቸውን ጠቁመው፤ የጤና ባለሙያዎች ህይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል በቫይረሱ ለተጠቁ ዜጎች የህክምና አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ገልጸዋል። በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎችን በጎበኘንበት ወቅት የጤና ባለሙያዎች "በኢቦላ ቫይረስ ትያዛላችሁ" የሚል ስጋት እንደነበረባቸው ገልጸው፤ "ለእኛ አትጨነቁ፤ አታስቡ። እናንተ በየቀኑ ህይወታችሁን አደጋ ላይ በመጣል እየሰራችሁ ስለሆነ የእኛ ጉብኝት ምንም ሊያሳስባችሁ አይገባም" የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ተናግረዋል። የኢቦላ ቫይረስ ክስተት በጣም አደገኛ እንደሆነ የህክምና ባለሙያዎቹ መግለጻቸውንም ነው ዶክተር ቴድሮስ የተናገሩት። በዴሞክራቲክ ኮንጎ የከተማ አካባቢዎች ቫይረሱ መታየቱ አሳሳቢ ቢሆንም እ.ኤ.አ በ2014 ከነበረው በተሻለ የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅም መኖሩን አመልክተዋል። በአገሪቱ በቫይረሱ ለተጠቁት ዜጎች ዛሬ ክትባት መስጠት መጀመሩን ጠቁመው፤ የዓለም ጤና ድርጅት የስራ ክፍሎች በቅንጅት በመስራት ቫይረሱን ለመከላከል እያደረጉ ያለውን ጥረትም አድንቀዋል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና አጋር የጤና አካላት ቫይረሱ ሲከሰት ለሰጡት ፈጣን ምላሽ ምስጋና አቅርበዋል። ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ባለፉት 12 ወራት በ47 አገሮች በተከሰቱ 50 ድንገተኛ የጤና ጉዳዮችና ክስተቶች ምላሽ መስጠቱንም አክለዋል። በአጠቃላይ በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ በሽታዎችን በዘላቂነት ለመከላከል በየአገሮቹ ጠንካራ የጤና ስርአት መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። በአጠቃላይ በሽታዎችን ለመከላከል የፖለቲከኞች ቁርጠኝነትና ውሳኔ ሰጭነት፣ የአጋር አካላት ትብብርና "የአገሮችን የበሽታ መከላከል አቅም መገንባትና ጠንካራ የጤና ስርአት በየአገሮቹ መዘርጋት ያስፈልጋል" ብለዋል። እስከ ግንቦት 18 ቀን 2010 ዓ.ም በሚቆየው የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት 71ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የድርጅቱ አባል አገሮች በዓለም አቀፍ የጤና ደንቦች ተፈጻሚነት፣ በድንገተኛ ህክምና አሳጣጥና አደጋ ምላሽ፣ በክትባት አቅርቦትና መድሐኒቶች እጥረት፣ በፖሊዮ ቫይረስ ወቅታዊ ሁኔታ፣ የአየር ንብረት ለውጥና ጤና ትስስር ዙሪያ በዋንኛነት እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም