የኢትዮጵያና የኤርትራን ወዳጅነት ለማጠናከር በተዘጋጀው የጎዳና ላይ ሩጫ ህዝቡ በነቂስ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የኤርትራን ወዳጅነት ለማጠናከር በተዘጋጀው የጎዳና ላይ ሩጫ ህዝቡ በነቂስ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ
ባህር ዳር ጥቅምት 6/2011 በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ወዳጅነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማገዝ በሚካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ ኢትዮጵያዊያን በነቂስ በመውጣት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለጸ። በዋዜማ ፕሮሞሽንና ኢቨንት የተዘጋጀው የመጀመሪያው " ዶክተር አብይ-ኢሱ" የተሰኘው የሰባት ኪሎ ሜትር የፍቅር፣ የሰላም፣ የአንድነትና የአብሮነት የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ጥቅምት 25 ቀን 2011 ዓ.ም በአስመራና በአምስት የኢትዮጵያ ከተሞች ይካሄዳል። የዋዜማ ፕሮሞሽንና ኢቨንት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ብሩክ በቀለ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት ሩጫው በአስመራ፣ በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ሃዋሳ፣ አዳማና ጎንደር ከተሞች ነው የሚካሄደው። የሩጫው ዓላማ በግጭት ምክንያት ለዘመናት ተለያይተው የኖሩትን የሁለቱ አገራት ህዝቦች ዳግም ወደ ሰላም እንዲመጡ ከፍተኛ መስዋትነት የከፈሉትን የሁለቱን አገራት መሪዎች ለማመስገንና የሁለቱ አገራት ግንኙነት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልክት ለማስተላለፍ ነው። “ለዶክተር አቢ-ኢሱ” እሮጣለሁ በሚል መሪ ቃል ለተዘጋጀው ሩጫ ከ100 ሺህ በላይ ባለ 250 ብር የሩጫ ቲሸርቶች በመሸጥ ላይ መሆናቸውንም አቶ ብሩክ ገልጸዋል። ከቲሸርት ሽያጭ 30 በመቶው ለመንግስት በህጋዊ ደረሰኝ ገቢ እንደሚደረግም ጠቁመዋል። በሩጫ ውድድሩ ፕሮፌሽናል አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከአንድ እስከ ሦስት ለሚወጡ አሸናፊዎች የወርቅ፣ የብርና የነሀስ እንዲሁም የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከት ተገልጿል። የሁለቱ አገራት መሪዎች ለሰላምና ወዳጅነት ላሳዩት ቁርጠኝነት እውቅና ከመስጠት በተጨማሪ ግንኙነቱ ዘላቂ እንዲሆን ህዝቡ አጋርነቱን በሩጫው በመሳተፍ ማሳየት እንዳለበት ገልጸዋል። የኤርትራ ህዝብ ከወንድሙ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋራ የጀመረው የሰላምና የወዳጅነት መንፈስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሩጫው ልዩ ትርጉም ያለው በመሆኑ በእለቱ በአስመራ ከተማ በሚደረገው የሩጫ ውድድርም ኤርትራዊያን በነቂስ ወጥተው እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል። አቶ ብሩክ እንዳሉት የሩጫ ውድድሩን በአንድ ጊዜ በሁሉም የክልሉ ከተሞች ለማካሄድ የማይቻል በመሆኑ በመጀመሪያው ዙር ሩጫ የማይካሄድባቸው ትልልቅ የኢትዮጵያ ከተሞች በሁለተኛውና በሦተኛው ዙር ይካሄድባቸዋል። በመጪው ጥቅምት 25 ቀን 2011 ዓ.ም በአስመራና በአምስት የኢትዮጵያ ከተሞች ጠዋት 2፡00 ሰዓት ተኩል ላይ በተመሳሳይ ሰዓት በሚካሄደው የሩጫ ውድድር በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።