ጉባዔው አዲስ ከተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመስራት ተዘጋጅቷል - ኢዜአ አማርኛ
ጉባዔው አዲስ ከተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመስራት ተዘጋጅቷል
አዲስ አበባ 6/2011 የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አዲስ ከተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር ጋር ለመስራት መዘጋጀቱን አስታወቀ። ኢትዮጵያ በዓለም ቀዳሚ የሚያደርጋትን የሰላም ሚኒስቴር አቋቁማለች። ሰላም ማስፈንና የህግ የበላይነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ሚኒስቴሩ በትኩረት የሚሰራባቸው ጉዳዮች ናቸው ተብሏል። አዲሱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በአገር ውስጥና በቀጣናው የህግ የበላይነት አንዲሰፍንና ሰላም እንዲረጋገጥ ከመስራት ባለፈ ግለሰቦች ህግ እንዲያከብሩ ልዩነትም ሆነ ቅሬታ ሲኖራቸውም ህጋዊ ስነ-ስርዓት በመከተል መብትና ጥቅሞቻቸውን እንዲያስጠብቁ ያስገድዳል። ከባህልና ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሰራም ተነግሯል። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ ለኢዜአ እንደገለጹት የሰላም ስራ አንዴ ተሰርቶ የሚቆም አይደለም። በአገሪቷ ሰላም እንዲሰፍንና ልማት እንዲመጣ የሁሉም እምነት ተቋማት መሪዎች ተከታዮቻቸውን ስለ ሰላምና ልማት ማስተማር የዕለት ተዕለት ተግባራቸው መሆኑን አንስተዋል። ይህን ስራ የበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠልና በአገሪቷ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሰላም ሚኒስቴር መቋቋሙም አስፈላጊ ነው ይላሉ። ጉባኤው ቀደም ሲል ከፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስቴር ጋር ከግጦሽ መሬትና ከውሃ ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ ግጭቶችን ለመፍታት በጋራ ሲሰራ እንደነበርም አስታውሰዋል። በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ አይነት ግጭቶች እንዳይከሰቱ ይህ ሚኒስቴር መቋቋሙ ተገቢ መሆኑንም ነው መጋቢ ዘሪሁን የተናገሩት። ጉባዔውም ከአዲሱ የሰላም ሚኒስቴር ጋር በአገሪቷ ዘላቂ ሰላምና ልማት ጉዳይ ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል። የሰላም ሚኒስቴር የብሄራዊ ደህነነት መረጃ አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህነነት ኤጀንሲ፣ የፋይናንስ ደህነነት መረጃ ማዕከል፣ የፌዴራል ፖሊስ ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች መምሪያ፣ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች፣ ብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራርና የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ዓለም ዓቀፍ የሰላምና የልማት ኢንስቲትዩትን ስራ በበላይነት ይመራል።