ኤጀንሲው ከሰነድ አልባ መሬት ጋር ተያይዞ የሚታየውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመፍታት እየሰራ ነው

32
ነቀምቴ ግንቦት 13/2010 የነቀምቴ ከተማ  መሬት አስተዳደርና ልማት ኤጀንሲ ከሰነድ አልባ መሬት ጋር ተያይዞ የሚታየውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የኤጀንሲው ኃላፊ አቶ ገመችስ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለፁት በከተማው ከመሬት አስተዳደር ጋር ተያይዞ በነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ   በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር  ሆኖ ሲነሳ  ቆይቷል፡፡ ችግሩን ለመፍታት በጉዳዩ ዙሪያ በየደረጃው  ለሚገኙ ባለሙያዎችና የአመራር አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ከተሰጠ በኋላ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ኤጀንሲው ከ2005 በፊት የተያዘ ሰነድ አልባ መሬት ህጋዊ የማድረግ ስራ በማካሄድ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እስካሁንም በ165 ግለሰቦች ተይዞ ለነበረ ሰነድ አልባ መሬት ካርታና ኘላን ተዘጋጅቶ ለነዋሪዎች መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ የተጀመረው እንቅስቃሴ ሕገ ወጥ የግንባታ ስራዎችን ለመከላከልና ከተማዋ በፕላን እንድትመራ ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል። የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ አቶ መኮንን ፍቃዱ በሰጡት አስተያየት ለሰነድ አልባ ይዞታቸው ካርታና ኘላን መስጠቱ መንግስት በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ያለውን አጋርነት ያስመሰከረበት ተግባር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ያገኙት ካርታና ኘላን የስምንት ቤተሰባቸውን ህይወት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመምራት ዋስትና እንደሆናቸውም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም