በሩብ ዓመቱ ከ3 ነጥብ 21 ቢሊዮን ብር በላይ የአገር ውስጥ ታክስ ገቢ አልተሰበሰበም - ኢዜአ አማርኛ
በሩብ ዓመቱ ከ3 ነጥብ 21 ቢሊዮን ብር በላይ የአገር ውስጥ ታክስ ገቢ አልተሰበሰበም
አዲስ አበባ ጥቅምት 6/2011 በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ከታክሰ ይሰበሰባል ተብሎ የነበረ ከ3 ነጥብ 21 ቢሊዮን ብር በላይ የአገር ውስጥ ገቢ አልተሰበሰበም ተባለ። መላው ግብር ከፋይ ህብረተሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል አገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል። የፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እንዳለው በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከአገር ውስጥ ታክስ 28 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ያህል ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ማሳካት የተቻለው ግን ወደ25 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ነው። በሩብ ዓመቱ መስከረም ወር ብቻ ከአገር ውስጥ ታክስ ለመሰብሰብ የታቀደው 11 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሲሆን መሰብሰብ የተቻለው ግን ወደ 7 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ነው። የባለስልጣኑ የአገር ውስጥ ታክስ ፕሮግራም ልማትና ድጋፍ ስራዎች ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬከተር ወይዘሮ ነጻነት አበራ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ይህ ኃብት በወቅቱ ገቢ ሊደረግ ባለመቻሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችንና የሥራ ፈጠራ እቅዶችን ጨምሮ በመንግስት የተለያዩ ልማት ውጥኖች ላይ ችግር ይፈጥራል። የግብር አሰባሰቡ አፈፃፀም ዝቅተኛ የሆነው በሰብሳቢውና በግብር ከፋዩ ማህበረሰብ በኩል በሚታዩ የተለያዩ ችግሮች ምክንያት መሆኑንም ጠቁመዋል። የብቃት ማነስን፣ የህግ ማስከበር ስራ ደካማነት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እጥረትን ጨምሮ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት በኩል የሚያቱት ችግሮች የግብር አሰባሰቡ እንዳይሳካ ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው ሲሉ ወይዘሮ ነፃነት አብራርተዋል። ግብርና ታክስ መደበቅ፣ ደረሰኝ አለመጠቀም፣ አግባብ ያልሆኑ ቅሬታዎችን ማቅረብ እና የተከማቸ ዕዳ በጊዜው አለመክፈል ደግሞ በግብር ከፋዩ በኩል የሚስተዋሉ ፈተናዎች ናቸው ተብሏል። የተያዘው ጥቅምት ወር ከፍተኛ ገቢ የሚሰበሰብበት ወቅት በመሆኑ የሁለቱም ወገኖች የሚስተዋሉትን ክፍተቶች በመቅረፍ እቅዱን ለማካካስ ጥረት እንደሚደረግ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል። ላለፉት ሶስት ወራት መሰብሰብ ያልተቻለውን 3 ነጥብ 21 ቢሊዮን ብር ጨምሮ በጠቅላላው 23 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል። መላው ግብር ከፋይ ህብረተሰብም ከጥቅምት ወር 2011 ዓም በኋላ ቅጣት የሚከተል መሆኑን በማጤን የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል አገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። ግብር ከፋዩ ህዝብ ግብሩን በተገቢ ሰነድ በማስደገፍና ደረሰኝ በአግበቡ በመጠቀም በታማኝነት ያሳውቅ ዘንድም አስገንዝበዋል። ባለሰልጣኑ ዘርፉን በዘላቂነት በማዘመን የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና የተዋጣለት ለማድረግ ራሱን በሰው ኃይል ልማትና በቴክኖሎጂ እያደራጀ ነው ተብሏል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ ያፀደቀው ፌዴራል መንግስት በጀት 346 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ነው። ከዚህ ውስጥ ውስጥ ከ241 ቢሊዮን ብር በላዩን ከአገር ውስጥ ታክስና ከውጪ ንግድ ለመሰብሰበ አቅዶ እየሰራ ነው። ይህም 70 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን በጀት የሚሸፍን ነው።