በካቢኔው የሴቶች ተዋጽኦ ከወንዶች መስተካከሉ የአገሪቱን ልማት ለማፋጠንና ሌብነትን ለማስቀረት ይረዳል - ኢዜአ አማርኛ
በካቢኔው የሴቶች ተዋጽኦ ከወንዶች መስተካከሉ የአገሪቱን ልማት ለማፋጠንና ሌብነትን ለማስቀረት ይረዳል
አርባ ምንጭ ጥቅምት 6/2011 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባጸደቀው አዲሱ ካቢኔ የሴቶች ተዋጽኦ ከወንዶች ጋር መመጣጠኑ የአገሪቱን ልማት ለማፋጠንና ሌብነትን ለማስቀረት እንደሚረዳ የዓርባ ምንጭ ከተማ የኅብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ ፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸዉ አስተያየት ሰጪዎች እንደተናገሩት በአገሪቱ ካቢኔ የሴቶች ተዋጽኦ ከወንዶች ጋር መመጣጠኑ ልማትን ለማፋጠንና የሀብት ምዝበራን ለማዳን ያስችላል፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎቹ የጋሞ ጎፋ ዞን ምክር ቤት ምክትል አፌ-ጉባዔ ወይዘሮ አማረች በየነ በሰጡት አስተያየት ሹመቱ በኢትዮጵያ ታሪክ የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ሚና ዕድገት እየታየበት መምጣቱን ያሳያል ብለዋል። ሹመቱ በሴቶች ላይ የነበረውን የተሳሳተ አመለካከት በተግባር የተቀየረበት ልዩና ታሪካዊ ውሳኔ ነው በማለትም ገልጸውታል፡፡ ሴቶች በተፈጥሮአቸዉ ከኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ቁጥብ በመሆናቸው የአገሪቱን ሀብት ከሌብነት ለማዳን ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸዉም አፈ ጉባዔዋ አመልክተዋል ፡፡ በዓርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል መምህር ኢያሱ ማርቆስ በበኩላቸው ያለ ሴቶች ተሳትፎ ልማት ግቡን ስለማይመታ በካቢኔው የሴቶች ድርሻ ማደጉ የለውጥ ጉዞው ለማሳካት እንደሚያስችል ተናግረዋል ፡፡ በአገሪቱ ታሪክ ልዩ ገድል ያስመዘገቡ ጀግና ሴቶች እንደነበሩ አስታውሰው፣ ተሿሚዎቹ ሴት ሚኒስትሮች የኢትዮጵያን ልማት በማፋጠን ድርሻቸውን ይወጣሉ ብዬ እገምታለሁ ብለዋል፡፡ ሴቶች ተግባራዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ በኢትዮ ቴሌኮም የተጀመረዉን የአገልግሎት ሪፎርም ለአብነት የጠቀሱት ደግሞ የዓርባ ምንጭ ከተማ መናኸሪያ ቀበሌ አቶ መንግሥቱ ታሪኩ ናቸው፡፡ ሴቶች ለሕገ-መንግሥቱ ተገዢ በመሆንና አሳምኖ በመሥራት ረገድ ጥንካሬ እንደሚታይባቸውም ጠቁመዋል፡፡ በዓርባ ምንጭ ነጭ ሣር ክፍለ ከተማ የዕድገት በር ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ንግሥት ተፈራ በበኩላቸው ሴቶች ከቤት ጀምሮ ረዥም ጊዜያቸውን በሥራ የማሳለፍ ያላቸውን ልምድ ህዝባዊ ተልዕኮን ለመፈጸምም አያዳግታቸውም ብለዋል፡፡ መንግሥት የሴቶችን ተዋጽኦ ከወንዶች እኩል ማድረጉ ሴቶች በተግባር ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ያመላክታል ሲሉም ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባጸደቁት 20 የካቢኔ ሚኒስትሮች መካከል አሥሩን ሴቶች ናቸው።በኢትዮጵያ ታሪክም የመጀመሪያዋ የመከላከያ ሚኒስትር በዚሁ ካቢኔ ውስጥ ተካተዋል።