ቀጥታ፡

የንግድ ሚኒስቴርና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተዋሃዱ

አዲስ አበባ ጥቅምት 6/2011 ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ተነጣጥለው ሲሰሩ የነበሩት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተዋህደው እንደቀድሞው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሚል ተደራጁ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዘመን 4ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛው ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት የስራ አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን ተሻሽሎ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቀረበለትን የሚኒስትሮች ሹመት አፅድቋል። በዚህም ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሄር እንደ አዲስ የተዋቀረውን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር እንዲመሩ ተሹመዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የስራ አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን ተሻሽሎ የቀረበውን አዋጅ ቁጥር 1077/2011 በሙሉ ድምፅ አፅድቋል። መንግስት በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ አጎልብቶ ለማስቀጠል እንዲሁም በተቋማት ያለውን የሀብትና የሰው ሀይል በአግባቡ ለመምራት እንዲሁም የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመሰጠት እንዲቻል 28 የነበረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቢኔ አባላት ቁጥርን ወደ 20 ዝቅ እንዲል አድርጓል። በዚህም መሰረት የተለያዩ አዳዲስ የሚኒስቴር ተቋማት የተዋቀሩ ሲሆን ከዚህ በፊት ከነበሩት ሚኒስቴሮች የታጠፉና የተዋሃዱም አሉ። በዚህም በተናጠል ሲሰሩ የነበሩት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተዋህደው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሆኑ ተወስኗል። የፌዴራል አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ 691/2003 መሰረት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሚል ስያሜ በጋራ ሲሰሩ የነበሩ የሥራ ዘርፎች ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በሁለት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በተናጠል እንዲደራጁ ተደርገው እንደነበር ይታወቃል። በወቅቱ የንግድ ሚኒስቴር የንግድ ስርዓቱን ግልፅ፣ ተደራሽና ለውድድር የተጋለጠ እንዲሆን በማድረግ፣ ፍትሃዊ ንግድ በማስፈንና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በላቀ ደረጃ በማሳደግ የአምራቹን፣ የሸማቹንና የንግዱን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ነበር የተቋቋመው። የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠርና በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ድጋፍ ለማድረግና ዘርፉን ለማሳደግ የተቋቋመ ሚኒስቴር እንደነበር ይታወሳል። በሌላ በኩል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመዋሀድ የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሆን ወስኗል:: የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኤጀንሲ፣ ከኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኤጀንሲና ከቀድሞው የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር የመገናኛ ዘርፉን በማዋሃድ በ2003 ዓ.ም የተቋቋመ ተቋም ነበር። በስሩም የኢትዮ-ቴሌኮምንና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት  ድርጅትን ሲያስተዳድር ቆይቷል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበኩሉ በአዋጅ ቁጥር 604/2001 የተቋቋመ ሲሆን በስሩ አስራ አንድ ተጠሪ ተቋማት እንደነበሩት መረጃዎች ያመለክታሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም