ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስቴር አቋቋመች

አዲስ አበባ ጥቅምት 6/2011 ኢትዮጵያ በዓለም ቀዳሚ የሚያደርጋትን የሰላም ሚኒስቴር አቋቋመች። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የቀረበውና የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል። በዚሁ መሰረት የሰላም ሚኒስቴር የተቋቋመ ሲሆን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የነበሩትና ዛሬ ከዚህ የስራ ኃላፊነታቸው በፍቃዳቸው የለቀቁት ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል የአዲሱ ተቋም ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። አዲስ ከተቋቋሙት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አንዱ የሆነው የሰላም ሚኒስቴር ሰላምና የህግ የበላይነት በአገሪቱና በቀጠናው እንዲሰፍን ማድረግ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ ነው። ሚኒስቴሩ በስሩ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ የፌዴራል ፖሊስና የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከልን ያካትታል። እንዲሁም ቀደም ሲል ለፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስቴር ተሰጥቶ የነበረው ስልጣንና ተግባርም ተሰጥቶታል። በ1988 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩት በሚል ስያሜ የተቋቋመው ተቋም በ2008 ዓ.ም በአዲስ መልኩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነትና ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት በሚል መተካቱ ይታወቃል። የዚህ ተቋም ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ወይዘሮ ሙፈሪያት ከሚልም ላለፉት 6 ወራት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው አገልግለዋል። በምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ አወቃቀርና ሪፎርም ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጋቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ መስክረውላቸዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም