የስሎቫኒያው ፕሬዚዳንት ቦሩት ፓሆር የቅድስት ሥላሴ ካቴድራልንና ብሔራዊ ሙዚየምን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
የስሎቫኒያው ፕሬዚዳንት ቦሩት ፓሆር የቅድስት ሥላሴ ካቴድራልንና ብሔራዊ ሙዚየምን ጎበኙ
አዲስ አበባ ጥቅምት 6/2011 የስሎቫኒያው ፕሬዚዳንት ቦሩት ፓሆር የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ-ክርስቲያንና ብሔራዊ ሙዚየምን ዛሬ ማለዳ ላይ ጎበኙ። ፕሬዚዳንቱ ከትላንት ወዲያ ማምሻውን ነበር የሦስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ የገቡት። በትላንትናው ዕለትም ከፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በቤተ-መንግሥት ተወያይተዋል። በውይይታቸውም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለውን የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ቦሩት ፓሆር ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ጋር በነበራቸው ቆይታ በስሎቫኒያና በኢትዮጵያ መካከል የንግድ ትስስርን የሚያጠናክር የቢዝነስ ፎረም እንደሚደረግ መግለጻቸው ይታወሳል። ትስስሩን ለማጠናከርም ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የኢትዮጵያ ቢዝነስ ልዑክ ይዘው በስሎቫኒያን ጉብኝት እንዲያደርጉ ግብዣ አቅርበዋል። ፕሬዚዳንት ቦሩት ፓሆር በቅርቡ ስሎቫኒያ በአዲስ አበባ ኢምባሲዋን ለመክፈት እያጤነች መሆኑንም ጥቆማ ሰጥተዋል። ስሎቫኒያ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ አካል ስትሆን የአሁኑ የፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ጉብኝት በአገሪቱ መሪዎች ታሪክ ከሰሃራ በታች የተደረገ የመጀመሪያው ጉብኝት ነው