የፌደራል መንግሥትን አስፈጻሚ ተቋማትን ተግባርና ኃላፊነት ላይ የተደረገው ማሻሻያ ባለው የሰው ኃይል ላይ ተፅእኖ አይፈጥርም ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የፌደራል መንግሥትን አስፈጻሚ ተቋማትን ተግባርና ኃላፊነት ላይ የተደረገው ማሻሻያ ባለው የሰው ኃይል ላይ ተፅእኖ አይፈጥርም ተባለ
አዲስ አበባ ጥቅምት 6/2011 የፌደራል መንግሥት አስፈጻሚ ተቋማትን ተግባርና ኃላፊነት ለማሻሻል የቀረበው ሀሳብ በአሁኑ ወቅት በተቋማቱ ባለው የሰው ኃይል ላይ ተፅእኖ እንደማይፈጥር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የፌዴራል አስፈጻሚ አካልን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ በሰጡት ማበራሪያ እንዳሉት ተቋማቱ እንደገና እንዲደራጁ የተደረገው በአሁኑ ወቅት የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ስኬታማ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል ለማድረግ ነው። "ተቋም ማለት ሰውና በጀት ብቻ አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን የሚደረገው ማሻሻያ ዓላማው የሰው ኃይል፣ ሥራና በጀት መቀነስ ሳይሆን ያለውን ሁለንተናዊ ኃብት አቀናጅቶ በአግባቡ መጠቀም ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል። ማሻሻያው አገሪቱ በሁሉም ዘርፎች ለማሳካት የያዘቻቸውን ግቦች እውን ማድረግም የአዋጁ ዓላማ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። ማሻሻያው "ተቋማቱን እንደገና በማዋቀርና እንዲሰባሰቡ በማድረግ አገሪቱ አሁን ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ መሻገር የሚያስችሉ፣ ወቅቱን የሚመጥኑና ፣ በህዝብ የሚታመኑ ባህሪያትን የተላበሱ ተቋማትን የመፍጠር ዓላማ አለው" ብለዋል። ተቀራራቢ ዓለማና ግብ አንግበው የሚንቀሳቀሱ በርካታ ተቋማት ቢኖሩም በአገልግሎት መጓተት፣ የተጠቃሚ እርካታና ህዝብ የጣለባቸውን እምነት በወጉ የማይወጡ በርካቶች አሉ ሲሉም አብራርተዋል። አሁን እያገጠመ ያለው አፍፃጸም ጉድለትና በእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅዱ ላይ የሚታየውም ችግር ሁሉም ተቋም የተሰጠውን ስራ በአግባቡ አለመስራቱ መሆኑን ጠቅሰዋል። በመሆኑም በተቋም ደረጃም ሆነ በሌላ ቋሚ የሚባል ነገር ያለመኖሩን ገልጸው በየጊዜው ለውጥና እድገት ደረጃን መሰረት አድርጎ ተመሳሳይ ተቋማዊ የማሻሻያ እርምጃዎች እንደሚካሄዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል። የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በአዲሱ አደረጃጀት ወደኮሚሽንና መሰል አደረጃጀት መለወጣቸወን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁም ነገሩ የአደረጃጀተ ለውጡ ሳይሆን የስራው ደረጃ ትኩረት ማግኘት እንደሚገባም ገልጸዋል። የካቢኔ ቁጥርን መቀነስም በርካታ ወጪዎችን ስለሚቀንስ አሁን በአገር ደረጃ ላለው የፋይናንስ እጥረትን ይደጉማል ተብሎ እንደሚታመንም ጠቁመዋል። የፌዴራል አስፈጻሚ አካልን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው ረቂቅ አዋጅ መሰረት በአሁኑ ወቅት 28 የሆኑት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ወደ 19 ዝቅ ተደርገዋል። እነርሱም የሰላም ሚኒስቴር፣ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደዚሁም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ናቸው። በኮሚሽን ደረጃ የተቋቋሙት ደግሞ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ የአካባቢ ደህንነትና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ኮሚሽን፣ የፕላንና ልማት ኮሚሽንና የንቨስትመንት ኮሚሽን ናቸው። የምክር ቤቱ አባላት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በስፋት ከመከረ በኋላ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ አፅድቆታል።