ዓለም አቀፍ የቮሊቦል የአሰልጣኝነት ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ የቮሊቦል የአሰልጣኝነት ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል
አዲስ አበባ ጥቀምት 5/2011 ዓለም አቀፍ የቮሊቦል የሁለተኛ ደረጃ አሰልጣኝነት ስልጠና ዛሬ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ተጀምሯል። በሁለቱም ጾታዎች በአጠቃላይ 18 የቮሊቦል የአንደኛ ደረጃ አሰልጣኝነት ደረጃ ያላቸው አሰልጣኞች ይሳተፋሉ። ስልጠናውን የሚሰጡት የዓለም አቀፉ የቮሊቦል ፌዴሬሽን(ኤፍአይቪቢ) አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዓለማየሁ ሸዋታጠቅ ናቸው። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ሰልጣኞቹ በቆይታቸው የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና ይወስዳሉ። አሰልጣኞች ደረጃቸውን የሚያሳድጉበት ስልጠና በመሆኑም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። በስልጠናው ማጠናቀቂያ ወቅት የንድፈ ሀሳብና የተግባር ፈተና እንደሚሰጥ የገለጹት ኃላፊው ፈተናውን ያለፉ አሰልጣኞች ዓለም አቀፍ የቮሊቦል የሁለተኛ ደረጃ አሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት እንደሚያገኙም ጠቁመዋል። በቮሊቦል ስፖርት ውስጥ እንደ ዋነኛ ችግር የሚታየው ተተኪዎችን የማፍራት ችግር ለመፍታት አሰልጣኞቹ ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸውም ጠቅሰዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጨረሻው የቮሊቦል የአሰልጣኝነት ደረጃ ሶስተኛ ደረጃ የሚባለው እንደሆነም ነው አቶ ተክሉ ያስረዱት። ስልጠናው እስከ ጥቅምት 9 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።