በቅርሶች ላይ ዘላቂነት ያለው ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ የቅርስ ጥበቃ ፈንድ ሊቋቋም ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቅርሶች ላይ ዘላቂነት ያለው ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ የቅርስ ጥበቃ ፈንድ ሊቋቋም ነው
አዲስ አበባ ጥቅምት 5/2011 በኢትዮጵያ በቅርሶች ላይ ዘላቂነት ያለው ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ የቅርስ ጥበቃ ፈንድ ለማቋቋም ማቀዱን የብሔራዊ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ። ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላቸውና የአገሪቱ ህዝቦች ማንነት ነፀብራቅ የሆኑ አያሌ ተዳሳሽና የማይዳሰሱ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ባለጸጋ ብትሆንም ኃብቱ ተገቢው እውቅና፣ እንክብካቤና ጥበቃ እንዳልተደረገለት ባለሙያዎች ይገልፃሉ። ከእነዚህ ቅርሶች መካከል ተገቢው እንክብካቤ፣ ጥበቃና እድሳት በማጣታቸው በእድሜ ብዛት ለአደጋ እየተጋለጡ እንዳሉም ይነገራል። በባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ዘለቀ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለስልጣኑ አገሪቱ ካላት ሰፊ የቅርስ ሃብት አንጻር ከፌዴራል መንግስት በሚሰጠው ውስን የካፒታልና መደበኛ በጀት አስፈላጊውን የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ፍላጎት መሸፈን አቅም የለውም። አሁን ባለው የባለስልጣኑ አደረጃጀት የአገሪቱ ጥንታዊ ቅርሶች ከእድሜ ብዛት አደጋ እንዳይደርስባቸው አስፈላጊውን ጥናትና ምርምር፣ ጥበቃና እንክብካቤ እንደዚሁም ወቅታዊ ጥገና ለማድረግ በሚያስችል የሰው ኃይልና ፋይናንስ የተደራጀ አይደለም። ችግሩን ለመፍታትም በሌሎች አገሮች ተሞክሮ ጥናቶች ተደርገው በ2011 ዓ.ም ለቅርሶች ውጤታማ እንክብካቤና ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት እንዲኖረው የቅርስና እንክብካቤ ፍኖተ ካርታ ይዘጋጃል ብለዋል። በእቅዱ ምክረ ሃሳብም ባለስልጣኑ አሁን ባለበት የሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት ስለማይችል አደረጃጀቱ በኢንተርፕራይዝ መልክ ሆኖ የቅርስ ጥበቃ ፈንድ እንዲኖረው ለማድረግ መታቀዱን ገልፀዋል። መስሪያ ቤቱ የቅርስ ፈንድ አስተዳደር ከተቋቋመለት ከቱሪስት ገቢ ማግኘት ስለሚያስችለው የሚፈልገውን ሙያተኛ ለመቅጠር፣ ለቅርሶችም አስፈላጊውን በጀት መድቦ ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ እንደሚያስችለው ነው አቶ ኃይሉ የተናገሩት። ይህም ባለስልጣኑ በሰራተኛ ፍልሰት ላይ የሚያጋጥመውን የባለሙያ እጥረት ችግር ለመፍታት በሚፈልገው የሙያ ዘርፍ የሰው ኃይል ለማሟላትም ያግዘዋል ነው ያሉት።