ቀጥታ፡

የሰንደቅ ዓላማ ቀን በጅግጅጋ ከተማ ተከበረ

ጅግጂጋ  ጥቅምት 5/2011  “ሰንደቅ ዓላማችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን!” በሚል መሪ ቃል 11ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ ተከብሯል፡፡ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አደን ፋራህ  ለሰንደቅ ዓላማው ክብር በርካታ የክልሉ ተወላጆች የህይወት መስዋዕትነት መክፈላቸውንና ለሰንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብር በመስጠትና የህዝቡን ግንዛቤ በማሳደግ ሊሰራ ይገባዋል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሰንደቅ ዓላማ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦችና የሃይማኖት እኩልነትን እንደሚያንጸባርቅ ገልጸዋል። ሰንደቅ ዓላማው የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣የእምነትና የሥነ ልቡና የጋራ መገለጫ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ የክልል ምክር ቤቱ አፈጉባኤ አብዲ መሐመድ በበኩላቸው ሰንደቅ ዓላማ ዜጎች የጋራ ዓላማቸውን ለማሳካት እንደሚሰባሰቡት ገልጸው፣ ከ80 በላይ ቋንቋዎችና ዘጠኝ ክልሎች ባላት አገር ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለመፍጠር የጋራ ቋንቋቸው ሰንደቅ ዓላማቸው ነው ብለዋል፡፡ ገራድ ኮልሚዬ ገራድ መሐመድ በሰጡት አስተያየት በሰንደቅ ዓላማው መሃል ያለው ብሔራዊ ዓርማ የሶማሌ ክልል ሕዝብ ከሌሎች የአገሪቱ ሕዝቦች ጋር ያላቸውን እኩልነት እንደሚያንጸባርቅ አመልክተው፣ ሰንደቅ ዓላማውን ለመቀየር የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችና ግለሰቦች ህጋዊነቱን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል፡፡ በከተማው የቀበሌ 06 ነዋሪው አቶ ኤፍሬም ኢድሪስ በዓሉ በአገሪቱ ብሎም በክልሉ የለውጥ እንቅስቃሴ በተጀመረበት ጊዜ መከበሩ የተለየ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። በዓሉ በሰንደቅ ዓላማው ላይ ስላለው ብሔራዊ ዓርማ  ትርጉም ያወቁበት እንደሆነም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አሁን ባለው ቅርጽ ሥራ ላይ የዋለው ከ1880ዎቹ መጨረሻ ላይ ጀምሮ እንደሆነና ብሔራዊ ዓርማው አንዳንዴ መንፈሳዊ ሌላ ጊዜ ደግሞ ፖለቲካዊ ትርጓሜ ሲታከልበት መቆየቱ ተገልጿል፡፡ በበዓሉ ማጠቃለያ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ ሥርዓት አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም