በመስኖ የጓሮ አትክልት በማልማት ተጠቃሚነታችንን ለማጎልበት እየሰራን ነው -የምስራቅ ወለጋ አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
በመስኖ የጓሮ አትክልት በማልማት ተጠቃሚነታችንን ለማጎልበት እየሰራን ነው -የምስራቅ ወለጋ አርሶ አደሮች
ነቀምቴ ጥቅምት 5/2011 በበጋው ወቅት በመስኖ በመታገዝ የጓሮ አትክልቶችን በሁለት ዙር በማልማት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን በምስራቅ ወለጋ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች ገለፁ። የዞኑ የመስኖ ልማት ባለስልጣን በበኩሉ በበጋው ወቅት በመስኖ ለማልማት ከታቀደው መሬት ውስጥ 3ሺህ 579 ሄክታሩ ታርሶ በዘር መሸፈኑን አስታውቋል ፡፡ በዞኑ በሲቡ ስሬ ወረዳ የለሊሣ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዲንቁ ቱሉ በሰጡት አስተያየት በክረምት ዝናብ በ3 ሄክታር ማሳ ላይ በዋናነት በቆሎና ሌሎች ሰብሎችን በማልማት ምርታቸውን ከቤተሰብ ቀለብ ባለፈ ለገበያ ያቀርባሉ ። በበጋው ወቅት ደግሞ አንድ ሄክታር በሚጠጋ ማሳ ላይ በመስኖ በመታገዝ በሁለት ዙር የጓሮ አትክልት እንደሚያለሙ ተናግረዋል ። አርሶ አደሩ እንደሚሉት በክረምት ከሚያለሙት ሰብል ይልቅ በበጋው ወቅት በመስኖ ከሚያመርቱት የጓሮ አትክልት የተሻለ ገቢ እያገኙ ነው ። ባለፈው አመት በጋ ወቅት በመስኖ ካለሙት የጓሮ አትክልት ሽያጭ 20 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ። "በተያዘው በጋ ወቅት ልማቱን በማስፋፋት ገቢዬን የበለጠ ለማሳደግ እየሰራሁ ነው" ያሉት አርሶ አደር ዲንቁ በ1 ነጥብ 75 ሄክታር ማሳ ላይ ቲማቲም፣ ቀይ ሽንኩርትና ጥቅል ጎመን ለማልማት አቅደው በእርሻ ሥራ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል ። እንደ አርሶ አደር ዲንቁ ገለጻ የጓሮ አትክልት ልማቱን እያካሄዱ ያሉት የወንዝ ውሀን በሞተር ኃይል ስበው በመጠቀም ነው። "ያለፈው ልምዴን በመጠቀም በ1 ነጥብ 5 ሄክታር ማሳ ላይ ጥቅል ጎመንና ቲማቲም በመስኖ እያለማሁ ነው " ያሉት ደግሞ በጎቡ ሰዮ ወረዳ የኦንጎቦ በከኒሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ንጉሴ ተስፋዬ ናቸው። ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ጫላ ባንጃው በበኩላቸው በተያዘው የበጋ ወቅት በመስኖ በመታገዝ በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ ሽንኩርት ለማልማት አቅደው ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። "እስካሁን ግማሽ ሄክታሩን በዘር ሸፍኛለሁ፤ ከሁለት ሳምንት በኋላ ደግሞ በቀሪው ግማሽ ሄክታር ላይ ለመዝራት የማሳ ዝግጅት ላይ ነኝ" ብለዋል ። ባለፈው ዓመት በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ በመስኖ ካለሙት ቀይ ሽንኩርት ሽያጭ ከ30 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን አርሶ አደር ጫላ ተናግረዋል። የዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ቤኛ እንደገለፁት በተያዘው በጋ ወራት በ17 ወረዳዎች ባህላዊና ዘመናዊ ዘዴ በመጠቀም በሁለት ዙር 159 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል። እስካሁን ከታረሰው 6ሺህ 825 ሄክታር መሬት ውስጥ ግማሽ የሚሆነው በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ተክሎች መሸፈኑን ተናግረዋል። "በበጋው ወራት በመስኖ ለማልማት የታቀደው መሬት ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከለማው በ11ሺህ 356 ሄክታር ብልጫ አለው " ብለዋል ። ከዚህ ቀደም በአርሶ አደሩ እጅ የነበሩ 140 የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ተጠግነው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ ተጨማሪ 150 ሞተሮችን ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል። እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ በበጋው ወራት በመጀመሪያ ዙር በመስኖ ከሚለማው መሬት 13 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል፣ የስራ ስር፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። በወለጋ ዞን በ2010 የምርት ዘመን ከመስኖ ልማት ከ19 ሚሊዮን 643ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከባለሥልጣኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡