ቀጥታ፡

የሃገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር ማጠናከር ይገባል---ምሁራን

ሀዋሳ ግንቦት 13/2010 በሃገሪቱ ባለፉት ዓመታት የተመዘገበውን የምጣኔ ሀብት እድገት ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አመለከቱ፡፡ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአዋዳ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሃብታሙ ጌትነት ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት 20 ዓመታት በሃገሪቱ የተመዘገበው የምጣኔ ሀብት እድገት በአለም አቀፍ ደረጃም እውቅና የተሰጠው ነው፡፡ የምጣኔ ሀብት እድገቱ በምርታማነት  ሲለካ በማደግ ላይ ካሉ ሃገራት ፈጣን ቢሆንም ከእድገቱ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን በመመለስ ረገድ ግን ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ጤናማ የምጣኔ ሀብት እድገት የተረጋጋ፣ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ያለውና በደሃውና ሃብታሙ መካከል ያለው ልዩነት የጠበበ መሆን እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡ "ጤናማ ያልሆነ የኢኮኖሚ እድገት ባለሃብቱም ሆነ ሌላው ህብረተሰብ ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል" ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ባለሃብቱ ምክንያታዊ ለሆነ ገቢ በመስራት ደሃውን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡ አሁን በሃገሪቱ ያለው ለውጥ ጤናማ የኢኮኖሚ እድገት እንዲያመጣ አዳዲስ ፖሊሲዎች ሲቀረጹ ታች ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባና በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ  ተስፋአምላክ ግዛው በበኩላቸው " የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በየጊዜው እያደገ ቢመጣም እድገቱ ሁሉንም ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ መፈተሽ አለበት" ብለዋል፡፡ በኮንስትራክሽን፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫና በትላልቅ ግድቦች ላይ የሚታየው ለውጥ የሃገሪቱ እድገት ማሳያ መሆኑን የጠቀሱት ምሁሩ  በግብርናና በቱሪዝም መስክ የበለጠ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ " በሃገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር የአመራሩ ሚና ከፍተኛ ነው "ያሉት ደግሞ  በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ አዋዳ ኮሌጅ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተባባሪ ዲን ዶክተር ታምራት ሉደጎ ናቸው፡፡ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር መገርሳ ደበላ በበኩላቸው በሃገሪቱ የተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት በምርታማነት ሲለካ ለውጥ የታየበት ቢሆንም ከህብረተሰብ ተጠቃሚነት አንጻር በተገቢው እንዳልተሰራ ተናግረዋል፡፡ ፍትሃዊነትን በማረጋገጥ ከእድገቱ ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን  ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ላይ ማሻሻያዎችን ማድረግ  እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ምሁራኑ እንዳመለከቱት በሃገሪቱ ባለፉት ዓመታት የተመዘገበውን የምጣኔ ሀብት እድገት  ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር ቀጣይነት ባለው  አካሄድ ማጠናከር ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም