ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለመከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስልት እቀይሳለሁ ፡-ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን - ኢዜአ አማርኛ
ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለመከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስልት እቀይሳለሁ ፡-ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን
አዲስ አበባ ጥቅምት 5/2011 በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ዜጎች የሚያጋጥሟቸውን ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለመከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስልት ለመቀየስ ጥረት እንደምታደርግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገለፀች። የቤተክርስቲያኗ 37ኛ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዛሬ ሲጀመር ፓትሪያሪክ ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ባደረጉት ንግግር እንዳስተወቁት፤ ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ በአገሪቷ የተለያዩ ክፍሎች እየተባባሰ በመጣው ግጭት ሳቢያ በርካታ ዘጎች ከቀያቸው ተፈናቀለዋል፣ የሞትና የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት ደርሶባቸዋል። በተለይም በቅርቡ በሱማሌ ክልል አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውን፤ ካህናትና ምዕመናን ላይ ከባድ ጥቃት መፈፀሙን ፓትሪያርኩ አውስተዋል ፡፡ "በመሆኑም ቤተክርስቲያኗ በአምልኮ ቦታዋና ምዕመናን ልጆችዋ ላይ የሚደርሰውን አደጋ አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል የግንኙነት መረብ ትፈጥራለች" ብለዋል። ይህንንም ለማሳካት ከሚመለከታቸው የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ጋር የተቀናጀ የቅድመ ማስጠንቀቂያና መከላከያ ስልት የሚቀየስ መሆኑን ፓትሪያርኩ አስታውቀዋል። በአዲስ አበባ ዛሬ የተጀመረው የቤተክርስቲያኗ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በተለይም በአገራዊ አንድነት ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሏል። ከዚህም ሌላ ቤተክርስቲያኗ በምታከናውናቸው መንፈሳዊና የልማት ተራድኦ መርሃ-ግብሮች፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሃብት አጠባበቅና በቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ ውህደት ላይም ትኩረት ሰጥቶ ይነጋገራል።