ቀጥታ፡

የሰንደቅ ዓላማ አርማ ላይ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችሉ ስራዎች መስራት ይገባል

አዲስ አበባ ጥቅምት 5/2011 የሰንደቅ ዓላማ ዓርማ ላይ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችሉ ስራዎች መሰራት እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሰራተኞች ገለጹ። የሚኒስቴሩ ሰራተኞችና አመራሮች 11ኛውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል " ሰንደቅ ዓላማችን ለዲሞክራሲያዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ሃሳብ  በውይይት አክብረዋል። በውይይቱ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት በአገሪቷ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚገኘው አርማ ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት "ከሕብረተሰቡ ጋር በአግባቡ ውይይት አልተደረገበትም"። የዓርማው ትርጓሜን በተመለከተም ሕብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረውና አርማው የብሄር ብሄረሰቦች መገለጫ ሆኖ "ይወክለኛል የሚል የጋራ መግባባት አለመፈጠሩን" ተናግረዋል። ዓርማው በህግ ከመጽደቁ በፊት ከሕብረተሰቡ ጋር ውይይት ሳይደረግ "ከበላይ አመራሮች ተወስኖ ሕብረተሰቡ እንዲቀበለው ውሳኔ የተሰጠበት" መሆኑንም ነው የገለጹት። ከጸደቀ በኋላም የትምህርት ተቋማት ፣ ምሁራን ፣ የመገናኛ ብዙሃንና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ስለ ዓርማው ትርጓሜ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች በሚፈለገው መጠን አለመስራታቸውንም አንስተዋል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከአገሪቱ አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት የነጻነት ዓርማ ሲሆን በቅርብ ዓመታት ውስጥ ግን በአገሪቱ ተገቢው ክብር እየተሰጠው አይደለም ሲሉም ተናግረዋል። በመሆኑም በሰንደቅ ዓላማው ዓርማ ላይ የጋራ መግባባት ያለመፈጠሩንና በአንዳንድ አካባቢዎች የግጭቶች መነሻ እየሆነ መምጣቱንም ገልጸዋል። ይህንን ችግር ለመፍታትም ከሕብረተሰቡ ጋር  ጥልቀት ያለው ውይይት በማድረግና ህጋዊ ስርዓትን በመከተል የሕዝቡን ፍላጎት መለየት እንደሚገባ ከዚያም አልፎ አስፈላጊነቱ ታይቶ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ በበኩላቸው በባለድርሻ አካላት በኩል የሰንደቅ ዓላማ ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች በበቂ መጠን ባለመሰራቱ በቀጣይ ከሕብረተሰቡ ጋር ውይይት ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ይስማማሉ። በሕብረተሰቡ ዘንድ በአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማና በተፎካካሪ ፓርቲዎች ዓርማ  ልዩነት ላይ ጥርት ያለ ግንዛቤ ያለመኖሩንም ጠቅሰዋል። ይህንንም ችግር ለመፍታት መስራት እንደሚገባና ለሰንደቅ ዓላመውና ለብሄራዊ ዓርማው ተገቢውን ህጋዊ ክብር መስጠት ግዴታ መሆኑንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም