ቀጥታ፡

የቱኒዚያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ፣ ጨርቃጨርቅ እና የቆዳ ምርት ዘርፎች እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ

ጥቅምት 5/2011 የቱኒዚያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ፣ ጨርቃጨርቅ እና የቆዳ ምርት ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ቀረበ፡፡ የኢትዮ-ቱኒዝያ ቢዝነስ ፎረም ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ተካሂዷል:: የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት እና የቱኒዝያ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና የእጅ ጥበባት ማህበር በጋራ ባዘጋጁት ፎረም የሁለቱ ሃገራት ከ70 በላይ ኩባኒያዎች ተሳትፈዋል፡፡ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መብርሃቱ መለስ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ፎረሙ በሁለቱ አገራት ያለውን የንግድ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚረዳ ነው። የማኑፋክቸሪንግ፣ ጨርቃጨርቅ እና የቆዳ ምርት ዘርፎች ላይ አገራችን ቅድሚያ የምትሰጥ በመሆኑ በነዚህ ዘርፎች በጋራ ለመስራት ዶ/ር መብርሃቱ ጥሪ አቅርበዋል። የቱኒዝያ ኩባኒያዎች በማደግ ላይ ባለው የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ መዋዕለነዋያቸውን በማፍሰስ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ተናግረዋል። የቱኒዝያ ሪፐብሊክ የውጭ ንግድ ሚኒስትር ዴኤታ ሂቻም ቤን አህመድ በበኩላቸው የቱኒዝያው ልኡክ ለተደረገለት መልካም አቀባበል አመስግነው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ በጥምረት በመስራት የሁለቱን አገራት የንግድ ትስስር ማሳደግ እንድሚገባ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክትል ፕሬዝዳንት አሰፋ ገብረስላሴ በበኩላቸው የዚህ አይነት ፎረሞች መካሄድ የጋራ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነቱን ለማሳደግ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው የጥምረት ስራዎችን በማካሄድ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስሩን ማጠናከር እንደሚገባ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክትል ፕሬዝዳንት አሰፋ ገብረስላሴ እና የቱኒዝያ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና የእጅ ጥበባት ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አብደሳለም ሉኤድ የአገራቱን የንግድ ትስስር ለማጠናከር የጋራ መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም