የስሎቬኒያ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
የስሎቬኒያ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ጀመሩ
ጥቅምት 5/2011 የስሎቬኒያ ፕሬዝዳንት ቦሩት ፓሆር በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ይፋዊ ጉብኝት በይፋ ጀምረዋል። በስሎቬኒያ ፕሬዚዳንት ቦሩት ፓሆር የተመራና የስሎቬኒያ የቢዝነስ ማህበረሰብ አባላትን ያቀፈው ልኡክ የሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ነው ዛሬ አዲስ አበባ የገባው። ፕሬዚዳንት ቦሁር ዛሬ ረፋድ ከኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር በሁለቱ ሀገራት ወቅታዊና የወደፊት የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትብብር ዙሪያ ይወያያሉ ። ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች የጋራ አጀንዳ በሆኑ አካባቢያዊና አለም አቀፋዊ አጀንዳዎች ላይ በሚተባበሩበት ሁኔታም እንደሚመክሩም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ፕሬዚዳንት ፓሆር በቀጣይ ቀናት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤና ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ጋር ውይይቶች እንደሚያካሂዱ ታውቋል። ከፕሬዚዳንቱ ጋር የመጡት የስሎቬኒያ የንግድ ማህበረሰብ አባላትም ከኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና ከአገራችን የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር ስለ ንግድ አማራጮችና በአጋርነት መስራት ስለሚቻልበት ሁኔታ ውይይት ያካሂዳሉ።