ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጋሞ ጎፋ ዞን ነዋሪ ተወካዮች ጋር ዛሬ ይወያያሉ

171
አርባምንጭ ጥቅምት 4/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጋሞ ጎፋ ዞን ነዋሪ ተወካዮች ጋር ዛሬ ከሰዓት እንደሚወያዩ ተገለጸ። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንዲሪያስ ለኢዜአ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከሰዓት በአርባምንጭ ፓራዳይዝ ሎጅ ተገኝተው ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ይወያያሉ፡፡ የጋሞ አባቶች  ግጭትን ለመፍታት ላሳዩት የሰላም ተምሳሌትነትም እውቅና እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ በአርባ ምንጭ ከተማ በተከሰተው ግጭት የሃገር ሽማግሌዎች ግጭቱን ለመመከት እርጥብ ሳር ይዘው ወጣቶችን በመማጸናቸው ግጭቱ መርገቡን አስታውሰዋል፡፡ የእውቅና ስነ-ስርዓቱ ይህንን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም የጋሞ ጎፋ ዞን ህዝብና መንግስት በሃገሪቱ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለማስቀጠል የድርሻቸውን ለመወጣት ቃል የሚገቡበት ፕሮግራም እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ በፕሮግራሙ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ ሴቶችና የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ 400 የሚጠጉ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚያወያዩ ጠቁመዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሶስት ስኳር ፋብሪካ ግንባታን በይፋ መርቀው ከፍተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም