ሰንደቅ አላማ አንድነትን የሚያጠናክር እንጂ የግጭት መነሻ መሆን የለበትም - ኢዜአ አማርኛ
ሰንደቅ አላማ አንድነትን የሚያጠናክር እንጂ የግጭት መነሻ መሆን የለበትም
ጥቅምት 4/2011 ሰንደቅ አላማ አንድነትን የሚያጠናክር እንጂ የግጭት መነሻ ሊሆን አይገባም ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ የመዲናዋ ነዋሪ ወጣት አየነው መልካሙ እንዳለው ሰንደቅ አላማ የአንድነት መገለጫ ሆኖ ሳለ አልፎ አልፎ ለግጭቶች መነሻ ሲሆን ይሰተዋላል። መንግስታት ሲቀያየሩ ሰንደቅ አላማው ላይ የየራሳቸውን አርማ በማስቀመጣቸውና አርማው አይወክለንም የሚሉ ወገኖች በመኖራቸው ልዩነቱ ሊፈጠር ችሏልም ነው ያለው፡፡ ሰንደቅ አላማ የሀገርና የሕዝብ መገለጫ በመሆኑ የሚስተዋሉ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋልም ብሏል፡፡ ሀገራዊ ጉዳይን ዘንግቶ የተለያየ ሰንደቅ አላማ እየያዙ ፉክክር ውስጥ መግባት ለአላስፈላጊ ግጭት የሚዳርግ በመሆኑ ሁሉም የተስማማበት ሰንደቅ አላማ መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ አቶ አልታየ እንጥዋይ ናቸው፡፡ በአለም አደባባይ ጨምሮ በየትኛውም አጋጣሚ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ ሲያዩ በደስታ ብዛት እንባ እንደሚተናነቃቸውና የሀገር ኩራት እንደሚሰማቸውም ይናገራሉ፡፡ ወይዘሪት አለምአንቺ ተስፋዬ በበኩሏ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከጥንት ጀምሮ ለሃገር አንድነትና ሉዓላዊነት መስዋዕት የከፈለበት መሆኑን ትናገራለች። የሀገር ሰንደቅ አላማ በቀላሉ ሊታይ አይገባም የምትለው አለምአንቺ መንግስት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ምሁራን ህዝቡን ያሳተፈ ውይይት አድርገውበት እልባት ሊሰጠው ይገባልም ብላለች፡፡ የአርማና የሰንደቅ አላማን ትርጓሜ በውል ለይቶ አለማወቅ ለውዝግብ እየዳረገ መሆኑን የገለጸችው አለምአንቺ “ተፎካካሪ ፓርቲዎች የየራሳቸው አርማ ሊኖራቸው ይችላል፤ እንደ ሀገር ግን በሀገሪቱ ሰንድቅ አላማ ላይ ልዩነት ሊኖር አይገባም” ነው ያለችው ፡፡ ሰንደቅ አላማን እንደ ምክንያት በመጠቀም በህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚሞከሩ አካላት ለህገመንግስቱ ተገዥ መሆን ይኖርባቸዋል ብላለች፡፡ የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት በ1987 ዓ.ም ሲፀድቅ የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ እኩል አግድም የተሰመሩ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት መሀሉ ላይ አርማ ያለው እንዲሆን መደንገጉ ይታወሳል፡፡ የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ሐሳብ ለ11ኛ ይከበራል፡፡