ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ የቼስ ግራንድ ማስተር የሆነው እንግሊዛዊው ናይጅል ሾርት የፊታችን ረቡዕ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2010 ዓለም አቀፍ የቼስ ግራንድ ማስተር የሆነው እንግሊዛዊው ናይጅል ሾርት ከነገ በስቲያ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል። የቼስ ግራንድ ማስተርነት የዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን (ፊዴ) የቼስ ተወዳዳሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያስመዘግቡት ውጤትና በሚኖራቸው ስፖርታዊ ጨዋነት የሚሰጣቸው ከፍተኛ ማዕረግ ነው። የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ናይጅል ሾርት በአዲስ አበባ በሚኖረው የሁለት ቀናት ቆይታ ከፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ውይይት እንደሚያደርግና ቼስ በአገሪቷ ስላለው እንቅስቃሴ ገለጻ ይደረግለታል። ከመገናኛ ብዙሃንም ጋር ቆይታ እንደሚኖረውና በመዲናዋ የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችን ለማስጎብኘት እቅድ መያዙን ተናግረዋል። የናይጅል ሾርት ጉብኝት ኢትዮጵያ ከካስፓሮቭ የቼስ ፋውንዴሽን ጋር ባላት ግንኙነት መሰረት ፋውንዴሽኑ ያዘጋጀው እንደሆነ ጠቅሰዋል። የ52 ዓመቱ ናይጅል ሾርት የቼስ ግራንድ ማስተርነት ያገኘው በ19 ዓመቱ እ.አ.አ በ1984 ሲሆን በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የቼስ ውድድሮች አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል። ከቼስ ግራንድ ማስተርነቱ በተጨማሪ የቼስ ስፖርት አሰልጣኝ፣ በእንግሊዝ በሚገኙ ጋዜጦች የቼስ ስፖርት አምደኛና የቼስ ስፖርት ውድድሮች ዘጋቢ ሆኖ ይሰራል። የዓለም አቀፉ የቼስ ፈዴሬሽን እስካሁን ለ1500 የቼስ ስፖርተኞች የግራንድ ማስተርነት ማዕረግ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም