ተፈናቅለው በመጠለያ ከሚገኙ እናቶች 88ቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መውለዳቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ተፈናቅለው በመጠለያ ከሚገኙ እናቶች 88ቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መውለዳቸው ተገለጸ
ነቀምቴ ጥቅምት 3/2011 ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው በምስራቅ ወለጋ ዞን መጠለያ ጣቢያዎች ከሚገኙት ወገኖች መካከል 88 እናቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መውለዳቸውን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገለፁ። በምዕራብ ሸዋ ዞን የባኮ ቲቤ ወረዳ አስተዳደር በበኩሉ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 110 ኩንታል እህልና የተለያዩ አልባሳት ድጋፍ አድርጓል። የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪው አቶ ብርሃኑ በቀለ እንደገለፁት በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ 88 ነፍሰ ጡር እናቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለመውለድ ተገደዋል ። የምስራቅ ወለጋ ዞን የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት በየነ በበኩላቸው በሁከትና ብጥብጥ ዋነኛ ተጠቂዎች ሴቶችና ህፃናት መሆናቸውን ገልጸው ህብረተሰቡ ለሰላም መረጋገጥ በፅናት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል ። ህብረተሰቡ ለወላዶችና ለጨቅላ ህፃናቱ ተገቢውን ድጋፍና ክብካቤ በማድረግ ወገናዊ ተሳትፎውን እንዲያሳይም አሳስበዋል ። የምስራቅ ወለጋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሶናን ደሳለኝ በነቀምቴ ከተማ ከተጠለሉት እናቶች መካከል የወለዱና ለመውለድ በዘጠነኛው ወር የእርግዝና ጊዜ ላይ የሚገኙ እናቶች በነቀምቴ ሪፌራል ሆስፒታል አንድ አደራሽ ለብቻቸው ተዘጋጅቶላቸው አስፈላጊውን የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እናቶቹ በሆስፒታሉ ወጪ የምግብ፣ የአልጋ፣ የሳሙናና የማጠቢያ እቃዎች አገልግሎት ከማግኘታቸውም በተጨማሪ መንግሥት ከሚሰጣቸው ዕርዳታ ተገቢውን ምግብ እንዲያገኙ በመደረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል ። በሆስፒታል ከሚገኙት እናቶች መካከል ከሳሲጋ ወረዳ ሆረ ዋታ ቀበሌ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ የወለዱት ወይዘሮ በድሪያ ከሊፋ በሰጡት አስተያየት ልጃቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ ለመውለድ ቢገደዱም ሆስፒታሉና መንግስት እያደረገላቸው ባለው ድጋፍ መፅናናታቸውን ገልፀዋል ። ከሸምበሌሌ ቀበሌ የተፈናቀሉት ወይዘሮ ዓለሚቱ ሐምቢሣ በበኩላቸው "ተገቢውን ድጋፍና ክብካቤ እየተደረገልኝ ቢሆንም ግጭቱ የፈጠረብኝ ቀውስ ግን በቀላሉ የሚረሳ አየደለም" ብለዋል ። ከበሎ ጀገንፎኢ ወረዳ ሶጌ ቀበሌ ተፈናቅለው በሽሽት ላይ እያሉ በመንገድ ላይ መውለዳቸውን የገለጹት ወይዘሮ አበባዬ ሙሉጌታ ከወለዱ በኋላ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ሆነው ረጅም መንገድ በእግር ለመጓዝ መገደዳቸውን ተናግረዋል ። በአሁኑ ወቅት የከፋ ችግርን አልፈው በነቀምቴ ሆስፒታል አስፈላጊውን የሕክምና ክትትልና እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በምዕራብ ሸዋ ዞን የባኮ ቲቤ ወረዳ አስተዳደር ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 110 ኩንታል እህልና የተለያዩ አልባሳት ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል። የባኮ ቲቤ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ከበደ ደበሎ ለኢዜአ እንደገለፁት ወረዳው ከሾቦካ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ትናንት ድጋፍ ያደረገው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞንና በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች በተፈጠረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ነው። በእዚህም 60 ኩንታል ዱቄት ፣ 50 ኩንታል በቆሎ እንዲሁም የተለያዩ አልባሳትና ብርድ ልብስ ድጋፍ አድርጓል ። አቶ ከበደ እንዳሉት መስተዳድሩ ያደረገው የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ከ200 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ነው። ተፈናቃዮቹ በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ የወረዳው አስተዳደርና ህዝቡ ከጎናቸው እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል ። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የመተጋገዝና የመተባበር ባህሉን መሰረት በማድረግ ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን በተግባር እንዲያረጋግጥም ጥሪ አቅርበዋል ።