የኢትዮጵያ ዘመናዊ ህንፃዎች የአገሪቱን ባህልና የማንነት አሻራ የሚያንፀባርቁ አይደሉም ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ህንፃዎች የአገሪቱን ባህልና የማንነት አሻራ የሚያንፀባርቁ አይደሉም ተባለ
አዲስ አበባ ጥቅምት 3/2011 በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተገነቡትም ሆነ እየተገነቡ ያሉት አብዛኛዎቹ ዘመናዊ ህንፃዎች የአገሪቱን የባህልና የማንነት አሻራ የሚያንፀባርቁ አይደሉም ተባለ። ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች በተለይም በመዲናዋ አዲሰ አበባ ዓይንን የሚማርኩትን ጨምሮ በርካታ ህንጻዎች በመገንባት ላይ ናቸው። ይህም የአገሪቱን ህዝቦች ባህል፣ ታሪክና አኗኗር ጨምሮ የተለያዩ ልዩ ገፅታዎቿን ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚያስችል ቋሚ ኪነ-ህንፃ ጥበብን ለመጠቀም የሚያስችል መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ነበር። ሆኖም ግን የኪነ-ህንፃ ባለሙያዎች እንደሚሉት አብዛኛው የተገነባውና በመገንባት ላይ የሚገኘው ህንፃ ባለቤቶች ለዚህ አገራዊ ፋይዳ ያለው ጉዳይ ብዙም ትኩረት አልሰጡም። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በኪነ-ህንፃ ጥበባቸው ብቻ በሚሊዮን የሚቆጠር የዓለም ጎብኚዎችን መሳብ የቻሉ በርካታ አገራት መኖራቸውን የሚናገሩት ባለሙያዎቹ ኢትዮጵያ ግን ይህንን እድል እየተጠቀመችበት አይደለም ይላሉ። በዚህ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉ የኪነ-ህንፃ ባለሙያዎቹ አቶ ሽመልስ ጥላሁን እንዳሉት"በአገሪቱ እየተገነቡ ያሉ ህንፃዎች ትርጉም አልባ፣ የሀገርን ገጽታ የማያስተዋውቁና የቱሪስት መስህብ ለመሆን የሚበቁ አይደሉም"' ይላሉ። "አሁን እየተገነቡ ያለው ግንባታዎች የማንነት አሻራን የሚያንጸባርቁበት መልክ የለም ፤ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት እየተሰሩ ያሉት የውጪውን ትሬድ ነው ቀጥታ አገራችን ላይ የሚተገበረው˝ ያሉት ደሞ አቶ ወንዱወስን ሽመልስ ናቸው፡፡ የፌደራል መንግስት ህንጻዎች የግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈጠነ ጌታው በበኩለቸው፤የተገነቡትም ሆኑ እየተገነቡ ያሉ ህንፃዎች አብዛኖቹ የአገር ባህልና ታሪክ የማይንፀባረቅባቸው መሆኑን ይጋራሉ። የፌደራል መንግስት ህንጻዎች የግንባታ ሥራ የሚከወነው ህንጻዎቹ የሚሰጡት አገልግሎትን መሰረት በማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። ሆኖም ወደፊት የሚገነቡ የመንግስት ተቋማት ህንጻዎች የሀገርን ገጽታ ለሚያስተዋወቅና እና የቱርስት መስህብ ሊሆኑ በሚችሉበት መልኩ ለማስገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ይናገራሉ። በተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ወደፊት የሚታሰቡ ህንፃዎች የአገርን ባህልና ታሪክ መሰረት ባደረገ ኪነ-ህንፃ ቢታነፁ ከአገር አልፎ ባለንብረቶቹም ተጠቃሚ ይሆናሉ፤ በመሆኑም የሚመለከተው የመንግስት አካል፣ ባለኃብቱና የዘርፉ ሙያተኞቸ ጉዳዩን ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ሲሉም አስተያየተ ሰጪዎቹ አሳስበዋል።