ቀጥታ፡

ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ኃላፊነታችንን እንወጣለን-- ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

ባህር ዳር ጥቅምት 3/2011 በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ቅድሚያ በመስጠት ኃላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉ ሦስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች አስታወቁ። የአርበኞች ግንቦት ሰባት፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ከዳር እንዲደርስ መንግስትን ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልፀዋል። የአረበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንደገለፁት በኢትዮጵያ የነበረውን አፋኝ የፖለቲካ ሁኔታ ለመቀልበስ ጦርነትን እንደ አማራጭ መውሰዳቸውን አስታውሰዋል። ህዝቡ በየደረጃው የሚደርስበትን የአስተዳደር በደልም መሸከም ባለመቻሉ ለለውጥ በተደረገው ትግል በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ አስፈሪና አደገኛ ሁኔታ ተፈጥሮ መቆየቱን ገልጸዋል ። የህዝቡ በተለይም የወጣቱ ትግል ፍሬ አፍርቶና በለውጥ ኃይሎች ታግዞ በሃገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ በመታየቱ በውጭ አገርም ሆነ በሃገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲንቀሳቀሱ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል ። "በለውጥ ኃይሎች የተገኘውን ነፃነት በመጠቀም በሀጋሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ቅድሚያ በመስጠት ከመንግስት ጋር መስራት ግድ ይለናል"ብለዋል። ፓርቲዎች ስለ ፖለቲካ ድርጅታችን፣ ስለ ምናራምደው ፕሮግራምና ስለ ማንነትታችን ከማውራታችን በፊት ስለ ሰላምና መረጋጋት በአንድነት መስራትና አገርን ከጉዳት ቀድመን መታደግ ይጠበቅብናል" ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል። ምክትል ፕሬዚዳንቱ "ተፎካካሪ ፓርቲዎችና መንግስት ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት፣ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ በሚያስችሉን ጎዳዮች ላይ በህዝብ ፊት ቀርበን ስምምነት ልንፈራረምና ልንሰራ ይገባል" ሲሉም ተደምጠዋል። "በሃገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መብዛት ፋይዳ የለውም" ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ  በዓለም ላይ የፖለቲካ ርዕዮተ- ዓለም ከሦስት የማይበልጥ በመሆኑ ለሃገሪቱ የፖለቲካ እድገት ፓርቲዎች መቀራረብና ወደ አንድነት ሊመጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል። "አርበኞች ግንቦት ሰባትም ድርጅታዊ ማንነታችን አፍርሰንም ቢሆን ተመሳሳይና ተቀራራቢ የፖለቲካ ራዕይ ካላቸው ድርጅቶች ጋር ተዋህደን ከታች ወደ ላይ የሚያድግ ፓርቲ ለመመስረት ተዘጋጅተናል፤ በጉዳዩም ላይ ድርጅቶችን እያነጋገርን እንገኛለን" ብለዋል ምክትል ፕሬዚዳንቱ። ንቅናቄው አገራዊ ለውጡ እያደገ እንዲመጣ ለውጡን ከጀመሩ ኃይሎችና ከመንግስት ጋር ተቀራርቦና ተግባብቶ በመስራት አገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል። የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዴት መስፋት እንዳለበትና የህግ የበላይነት በምን አግባብ መከበር እንዳለበት ማስተማር ይገባል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫኔ ከበደ ናቸው። "በገዥው ፓርቲ ብቻ የዴሞክራሲ ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል" ያሉት ፕሬዚዳንቱ በሰጥቶ መቀበል መርህ ልዩነትን ለማጥበብና ለአሃገር አንድነት ጠንካራ ህብረት ፈጥሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል። "የአገር ውስጥ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምስረታ በመርህና በእውቀት ሳይሆን በኩርፊያ የተመሰረተ ነው ያሉት" ፕሬዚዳንቱ ከብዛት ወደ ጥራት በመምጣትና አገርን በዘላቂነት የሚጠቅም ሃሳብ በማመንጨት ከገዥው ፓርቲ ጋር ተደምሮ ዴሞክራሲውን አንድ እርምጃ ማራመድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ በአገሪቱ የተጀመረው ፖለቲካዊ ለውጥ ለውጡን በማይፈልጉ ጥቂት ኃይሎች እንዳይደናቀፍ ኢዴፓ አቅሙ የቻለውን ሁሉ ይሰራል። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)  ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ በበኩላቸው መንግስት ህግን የማስከበር ስራውን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መስራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል ። "በየአካባቢው የሚስተዋለው መፈናቀል ለውጡን በማይፈልጉ ኃይሎች የገንዘብ ድጋፍ የተቀነባበረ ሴራ ነው" ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ የዜጎችን መፈናቀልም የለውጥ ኃይሉ አገር የመምራት አቅም እንደሌለውና ጠላትን መመከት እንደማይችል ማሳያ አድርገው እየተጠቀሙበት መሆኑን አብራርተዋል ። " ከመንግስትና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የተውጣጣ ጥምር ኃይል በማቋቋም በህዝቡ ውስጥ ድብቅ ፍላጎትና የቀረ ስሜት ካለ በማወያየት መፍታት ይገባል" ብለዋል። አመጽ ሳይነሳ፣ ንብረት ሳይወድም፣ ዜጎች ሳይፈናቀሉና በህይወት የመኖር ስጋት ሳይፈጠር ለችግሮች በሰላማዊ መንገድ እልባት ማግኘት እንደሚቻል ዜጎችን ማስተማር ከሁሉም አንደሚጠበቅ አመልክተዋል። ህዝቡ የተለየ ዓላማ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ተከታትሎ እንዲያጋልጥና በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ከመንግስት ጎን ሆኖ እንዲሰራም ጠይቀዋል ። እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ መኢአድ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ በመጠቀም በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠርና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከመንግስት ጎን ሆኖ ይሰራል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም