የአገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ፋብሪካዎች የገበያ ድርሻ አናሳ ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የአገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ፋብሪካዎች የገበያ ድርሻ አናሳ ነው ተባለ
አዳማ ጥቅምት 3/2011 የአገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ፋብሪካዎች የገበያ ድርሻ በዘጠኝ እጥፍ እድገት ቢያሳይም ተሳትፏቸው ከ20 በመቶ የበለጠ አይደለም ተባለ። ፋብሪካዎቹ በበኩላቸው "የችግራችን ዋና ምንጭ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው"ብለዋል። በኢትዮጵያ መድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የመድኃኒትና የሕክምና መሳሪያዎች ክምችትና ስርጭት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዓለም አድራሮ ለኢዜአ እንደገለጹት የሀገሪቱ ዓመታዊ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች የግዥ አፈጻጸም ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ አድጓል። በስርጭት በኩልም ባለፈው ዓመት 16 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች በመላው አገሪቱ ለሚገኙ የጤና ተቋማት እንዲዳረሱ መደረጉን ነው የገለጹት። እንደ አቶ ተስፋዓለም ገለጻ መድኃኒትና መሳሪያዎቹ 80 ከመቶ ከውጭ 20 ከመቶ ደግሞ ከአገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ፋብሪካዎች ተገዝተው የሚቀርቡ ናቸው። ከእዚህ አንጻር የአገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ፋብሪካዎች የማቅረብ አቅማቸው ባለፉት ዓመታት በዘጠኝ እጥፍ ቢጨምርም እንዲያቀርቡ ከሚፈለገውና በየዓመቱ ከሚሰጣቸው የግዥ ትእዛዝ አንፃር አፈጻጸማቸው አሁንም ከግማሽ አለመዝለሉን ተናግረዋል። ለአብነትም ባለፈው ዓመት የ821 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያ እንዲያቀርቡ የግዥ ትእዛዝ ቢሰጣቸውም ማቅረብ የቻሉት የ491 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን አስረድተዋል። "በአምራቾቹ ደካማ አፈጻጸም ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን እጥረት ለመከላከል ሲባል ኤጀንሲው የትዕዛዙን ግማሽ ለውጭ አቅራቢዎች ለመስጠት ተገዷል" ብለዋል ። እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ የአገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ፋብሪካዎችን ለማበረታታት ያለተቀናቃኝ የሚሳተፉባቸው ከ100 በላይ መድኃኒቶች ዝርዝር ተለይተው ቀርበዋል። ጨረታውን ሲያሸንፉም የገንዘብ እጥረት እንዳይገጥማቸው 30 በመቶ የቅድመያ ክፍያ እንዲሰጣቸውና ሌሎች ድጋፎች እየተደረጉ ቢሆንም ውጤቱ አጥጋቢ አለመሆኑን ነው የተናገሩት ። ስኬታማ እንዲሆኑ በተለያየ መንገድ ቢደገፉም በገቡት ውል መሰረት መንቀሳቀስ አለመቻላቸው በመድኃኒት በሕክምና መሳሪያዎች አቅርቦት ላይ የጎላ ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል። መንግስት በአጭር ጊዜ ዕቅዱ ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚሆነውን የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ግዥ በአገር ውስጥ የመሸፈን ፍላጎት ያለው በመሆኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልበትም አቶ ተስፋ ዓለም አመልክተዋል ። ፋብሪካዎች በበኩላቸው ጥቃቅን ችግሮቻቸው በሂደት በራሳቸው አቅም እንደሚፈቱት ቢናገሩም የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለአፈጻጸማቸው ማነስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል። የአገር ውስጥ የመድኃኒትና የህክምና መገልገያ አምራቾች ዘርፍ ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙከሚል አብደላ ስለሁኔታው ተጠይቀው እንዳሉት መድኃኒት ለማምረት የሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎችን ለመግዛት የውጭ ምንዛሬ በሚፈለገው መጠንና ጊዜ እንደማይገኙና ይህም በአፈጻጸም ላይ ተፅእኖ አሳድሮባቸዋል። የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ከድር ሸሪፍ በበኩላቸው "አምና ለጥሬ ዕቃና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ግዥ የሚሆን 21 ሚሊዮን ዶላር ጠይቀን ከ11 ወራት ጥበቃ በኋላ የተሰጠን 5 ሚሊዮን ዶላር የማይሞላ ነው" ብለዋል ። ካለባቸው አጠቃላይ ችግር 85 በመቶ የሚሆነው ከውጭ ምንዛሬ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ይህ ችግራቸው ከተፈታ ሌሎች ጥቃቅን ችግሮችን በውስጥ አቅም በማስተካከል ውጤታማ መሆን አያቅተንም ሲሉ ተናግረዋል ። የአዲስ መደኃኒት ፋብሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅና የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዮናስ ገብረጻዲቅ በበኩላቸው "ዋነኛው ችግራችን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመሆኑ መንግስት ሁኔታውን ከግምት ውስጥ በማስገባት መፍትሔ ከሰጠን ስኬታማ እንሆናለን" ብለዋል ።