ቀጥታ፡

ሰላምን በማስጠበቅ ለሰንደቅ ዓላማ ያለንን ክብር በተግባር እናረጋግጣለን----በአፋር ክልል የፀጥታ አካላት

ሰመራ ጥቅምት 3/2011 የህዝብና የአገርን ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነታችንን በመወጣት ለሰንደቅ አዓላማ ያለንን ክብርና ፍቅር በተግባር እናረጋግጣለን ሲሉ በሰመራ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ የፀጥታ አካላት ገለፁ። 11ኛው የሰንድቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ አላማችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን" በሚል መሪቃል ትላንት በሰመራ ከተማ በፓናል በውይይት ተከብሯል። በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምስራቅ ዕዝ አባል ምክትል አስር አለቃ አስካለ ታደሰ  በሰጡት አስተያየት የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ የብሄር፣ ብሄረሰቦች እኩልነት ምልክት ነው ። "የመከላከያ ሠራዊት ከራስ በላይ ለሀገርና ህዝብ ሰላም ቅድሚያ የሚሰጥ በመሆኑ ኃላፊነቴን በአግባቡ በመወጣት ለሰንደቅ አላማ ያለኝን ክብርና ፍቅር በተግባር አረጋግጣለሁ" ብለዋል ። ዜጎች በሰንደቅ አላማ ጥላ ስር በመሆን የሀገራቸውን ልማትና እድገት ለማፋጠን በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባም ምክትል አስር አለቃ መክረዋል ። የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረባ ኮማንደር አብደላ አሊ በበኩላቸው ሰንደቅ አላማ የሉአላዊነት መገለጫ መሆኑን በመግለፅ አባቶች ለሰንደቅ አላማ ክብር ሲሉ የውጭ ወራሪን አሳፍረው መመለሳቸውን አስታውሰዋል ። እርሳቸው በተሰማሩበት መስክ የህዝብና የአገርን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ለሰንደቅ አላማ ያላቸውን ክብር እንደሚያረጋግጡ ተናግረዋል ። "በፌደራል ስርአቱም ሰንደቅ ዓላማ የሀገሪቱ ዜጎች እኩልነት፣ ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ነው" ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ። "የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው ህዝብ መገለጫ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝቦች የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ምልክት ጭምር ነው " ያሉት ደግሞ የክልሉ የመንግስት ሰራተኛ አቶ አብደላ ሃቢብ ናቸው ። "አዲሱ ትውልድም በፖለቲካ፣ በሃይማኖትና በዘር ሳይከፋፈል አገራዊ አንድነቱን በማጠናከር ለሰንደቅ ዓላማ ያለውን ክብርና ፍቅር ማረጋገጥ ይጠበቅበታል " ብሏል ። የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው ቀደምት አባቶቻችን በብሔርና በአምነት ሳይለያዩ የውጭ ወራሪ ኃይሎችንን አሳፍረው በመመለስና የሀገሪቱን ነጻነት በማስጠበቅ ለሰንደቅ አላማ ያላቸውን ክብር መግለጻቸውን አስታውሰዋል ። የአሁኑ ትውልድ ለሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ በንቃት በመሳተፍና አባቶች ያስረከቡትን አገር በመጠበቅ ለሰንደቅ ዓላማ ያለውን ክብር በተግባር ማሳየት እንዳለበት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል። በፓናል ውይይቱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራልና የክልል ፖሊስ አባላት አንዲሁም የመንግስት መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን በሰንደቅ ዓላማ ምንነት ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ፅሁፍ ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም