በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንዳይከሰት እየሰራን ነው--- የክልሉ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንዳይከሰት እየሰራን ነው--- የክልሉ አመራሮች
ጋምቤላ ጥቅምት 3/2011 በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም እንዳይከሰት በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ አመራሮች ገለጹ። ኮማንድ ፖስቱ በከተማዋ ተፈጠሮ የነበረውን የሰላም እጦት ችግር ወደ ተረጋጋ ሰላም ለመመለስ ባዘጋጀው የማስፈጸሚያ እቅድ ላይ ከዞንና ከወረዳ የአመራርና የጸጥታ አካላት ጋር ተወያይቷል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እንዳይከሰት በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። የአኝዋህ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኡጉታ ኡጁሉ በጋምቤላ ከተማ ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር በዞኑ እንዳይከሰት ትኩረት ተሰጥቶ መስራታቸውን ተናግረዋል። ተፈጥሮ ለነበረው ችግር መነሻ በማዕከል ያለ አመራር እንጂ ዞኖችና ወረዳዎች እንዳልሆኑ የጠቆሙት አስተዳዳሪው በክልሉ በተደጋገሚ እየተከሰቱ ያሉትን ችግሮች በዘለቄታው ለመፈታት አመራሩ እራሱን ሊፈትሽ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ በጋምቤላ ከተማ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ወደ ነበረበት ሰላም ለመመለስ በኮማንድ ፖስቱ ለተዘጋጀው የማስፈጸሚያ እቅድ ተግባራዊነት በትኩረት እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ የማጃንግ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሙሴ ጋጃክ ናቸው። የጋምቤላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኡጁሉ ኡሞድ በበኩላቸ በጋምቤላ ከተማ የተፈጠረው ችግር በወረዳው እንዳይከሰት ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት መደረጉንና በእዚህም ህዝቡ ያለምንም ስጋት ስራውን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይም ይህንኑ ተግባር በማጠናከርና በኮማንድ ፖስቱ የተፈጠረውን አደረጃጀት በመጠቀም በወረዳው ያለውን ሰላም ለማስቀጠል እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢና የክልሉ ርዕሰ መስተዳዳር አቶ ጋትሉዋክ ቱት በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በኮማንድ ፖስቱ የተዘጋጀውን የማስፈጸማያ እቅድ ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለእቅዱ ስኬታማነት መስራት ይገባል ብለዋል። በአገር መከላከያ ሠራዊት የ12ኛው ክፈለ ጦር አዛዥ ብርጋዴል ጄነራል ብረሃኑ ጥላሁን በበኩላቸው በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ የነበረውን የጸፅታ ችግር ወደ ተረጋጋ ሰላም ለመመለስ ለተዘጋጀው ዕቅድ ውጤታማነት በየደረጃው የሚገኘው አመራር ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በኮማንድ ፖስቱ የተዘጋጀውን ዕቅድ መነሻ በማደረግ በክልሉ የሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች የራሳቸውን ዕቅድ በማዘጋጀት ሊሰሩ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡