ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ክለቦች የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ዛሬ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ክለቦች የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ዛሬ ተጀመረ
አዲስ አበባ ግንቦት 13/2010 ከአምስት ክለቦች የተወጣጡ 79 ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ክለቦች የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ዛሬ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ተጀምሯል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ፣ ኦሮሚያ ፖሊስና የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የውድድሩ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው። የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አበባ አማረ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፤ ውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች በታዳጊና አዋቂ ነጠላ ጥንድ እና ድብልቅ በሚሉ ሰባት ዘርፎች ተከፋፍሎ ይካሄዳል። የውድድሩ ዋንኛ አላማ ለክለቦች የውድድር አማራጭ በማስፋት አቅማቸውን እንዲፈትሹ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። በዓመት ውስጥ የሚካሄዱትን የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድሮች ቁጥር ለማሳደግና ስፖርቱ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ለማድረግ የውድድሩ መካሄድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። በውድድሩ ላይ በእያንዳንዱ ዘርፍ አሸናፊ ለሚሆኑ ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት የሚበረከት ሲሆን የውድድሩ አሸናፊ ቡድን በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም የአፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ክለቦች ውድድር ላይ እንደሚሳተፍ ጠቁመዋል። የዘንድሮው ዓመት የመጀመሪያው የክለቦች ውድድር ባለፈው ጥር ወር በአፋር ክልል ተካሂዶ በአጠቃላይ ውጤት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማሸነፉን ወይዘሮ አበባ አስታውሰዋል። በተጨማሪም ከግንቦት 20 እስከ 26 ቀን 2010 ዓ.ም ዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳድሮች የሚሳተፉበት የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ከሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ጋር በመተባበር ለመወዳደር የሚፈልጉ አካላትን በሙሉ ማሳተፍ የሚችል የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ ከግንቦት 26 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ይከናወናል። የጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት ተጀመረ ተብሎ የሚጠቀሰው በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ቢሆንም እንደ አለም አቀፉ የጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን የመጀመሪያው ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር በድርጊት የተጀመረው እ.አ.አ በ1890 ሲሆን የስፖርቱ ፈጣሪ ዴቨድ ፎስተር የእንግሊዝ አገር ተወላጅ ነው።