በመንግስት ድጎማ የሚቀርበው ስኳርና ዘይት በተገቢው አይደርሰንም---የደብረብርሃን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በመንግስት ድጎማ የሚቀርበው ስኳርና ዘይት በተገቢው አይደርሰንም---የደብረብርሃን ነዋሪዎች
ደብረብርሃን ግንቦት13/2010 በመንግስት ድጎማ የሚቀርበው ስኳርና ዘይት በሰው ሰራሽ እጥረት ምክንያት በተገቢው እንደማይደርሳቸው በአማራ ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረብርሃን ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ። በከተማዋ የቀበሌ ሶስት ነዋሪ ወይዘሮ አለም ወንዱ ለኢዜአ እንዳመለከቱት በዘይትና ስኳር አቅርቦት ማነስ ምክንያት ለተጨማሪ ወጪ ተዳርገዋል፡፡ በመንግስት አቅርቦት ከቀበሌ 72 ብር የሚገዙትን ሶስት ሊትር ዘይት በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ከ160 ብር በላይ በድብቅ ለመግዛት መገደዳቸውን ጠቅሰዋል። የስኳርም ሆነ የዘይት አቅርቦት እስከ ሦስት ወር ድረስ እንደሚዘገይና ሲመጣም መጠኑ አንሷል በማለት በተገቢው ስለማይደርሳቸው መቸገራቸውን ተናግረዋል። የከተማዋ ቀበሌ ሁለት ነዋሪ አቶ አብራህም ተሰማ በበኩላቸው በየወሩ ይመጣ የነበረው ስኳርና ዘይት እስከ ሁለት ወራት ስለሚዘገይ ለችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ "ዘግይቶ ሲመጣም የተመደበውን ስኳርም ሆነ ዘይት ለመውሰድ ወረፋ ስለሚበዛ በስራችን ላይ ጫና እየፈጠረ ነው፤ከመጣ ከሁለት ቀን በኋላም ደግሞ አልቋል እያሉ በህገ-ወጥ መንገድ መልሰዎ አንድ ኪሎ በ50 ብር ይሸጡልናል" ብለዋል፡፡ " መንግስት በድጎማ የሚያመጣቸው ስኳር፣ ዘይትና የዳቦ ዱቄት የአቅርቦት ችግር ያለ ቢሆንም የስርጭት መበላሸቱ ደግሞ ችግሩን እንዲባባስ አድርጎታል "ያሉት ደግሞ በዞኑ ንግድ እና ኢንዱስትሪ መምሪያ የህጋዊ ስነልክ ባለሙያ አቶ ጥላሁን አበበ ናቸው። ሚዳ ወረሞ፣ኤፍራታና ግድም፣ቀወት፡አንጾኪያ ፣ጣርማ በር ወረዳዎች እና ደብደረብርሃን ላይ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴው ጎልቶ የታየባቸው አካባቢዎች እንደሆኑም ጠቁመዋል። በዚህ ድርጊት የተገኙ 43 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመስርቶ በ41 ግለሰቦች ላይ እስከ 8 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና እስከ 75 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት በፍርድ ቤት የተወሰናባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እርምጃው የተወሰደው ከተለያዩ የህብረተሰቡ ክፍሎችና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው ክትትል በማድረግ በተገኘ መረጃና ጥቆማ መሰረት እንደሆነም አመልክተዋል። በተጨማሪም በተቋቋመው የአስወጋጅ ግብረ ኃይል አማካኝነት 41 ዓይነት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የኢንዱስትሪ፣ የግብርናና ለስላሳ መጠጥ ምርቶችም እንዲወገዱ መደረጉን አቶ ጥላሁን አስረድተዋል፡፡ "በቅርቡም ለእርዳታ የመጣ ከ50 ኩንታል በላይ የተበላሸ በርበሬ፣ ከ3 ሺህ ሊትር የሚበልጥ ነዳጅና 1 ሺህ 400 ኪሎ ግራም የስንዴ ዱቄት በነጋዴዎች ሊሸጥ ሲል ተይዟል" ብለዋል፡፡ የተጀመረው የህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባርም ህብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኦፊሰር ምክትል ኮማንደር ወርቅአገኘሁ ሸዋ በበኩላቸው በህገ ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን በመጠቆም የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ በተለይ ወጣቱ፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ነጋዴው ከህግ አስከባሪዎች ጋር በመቀናጀት እየተበራከተ የመጣውን ህገ ወጥ ንግድ ለማስቆም የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡