ቀጥታ፡

ሰላምን ለማስፈን ለግጭት የማይተባበር መልካም ዜጋ ማፍራት ይገባል----መምህራን

ጥቅምት 3/2011 በሃገሪቱ ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈንና የዜጎችን መፈናቀል ለመግታት ለግጭት የማይተባበር በመልካም ስነምግባር የታነጸ ዜጋ ማፍራት እንደሚገባ በመዲናዋ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የስነምግባርና ሲቪክስ መምህራን ገለፁ፡፡ በሃገሪቱ ሰላም ማስፈን ለመንግስት የሚተው ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በወይዘሮ ቀለም ወርቅ መሰናዶ ትምህርት ቤት የስነምግባርና ሲቪክስ መምህር ተክለእየሱስ ግዛው እንዳሉት በሃገራችን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተወልደው ካደጉበትና ሃብት ካፈሩበት ቀዬ  መፈናቀላቸው የሚፀፅት ጉዳይ ነው ፡፡ በተለይም ግጭትን ለመቀስቀስና ዜጎችን ለማፈናቀል በገንዘብ መደለል ግብረገብነት የጎደለው ምግባር መሆኑን ገልፀው ስልጣን ለያዘው ሰው ከበሬታና ጊዜ መስጠት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ሃገሪቱ የያዘችውን የለውጥ ጉዞ ማደናቀፍና ህዝብን ቀውስ ውስጥ መክተት በታሪክ ውስጥ ተወቃሽና ለፀፀት የሚዳርግ ተግባር መሆኑንም  ነው ያወሱት፡፡ “ሰላም ለእኔም ይጠቅማል ፣ የእኔም ነው የሚል በጎ አስተሳሰብ መያዝ ይገባል” ያሉት መምህሩ ሰላም ከራስ አልፎ ለሌሎች ሃገራት እንዲተርፍ ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት ብሎ ማሰብ ይገባል ብለዋል፡፡ የቤተልሄም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሃብታሙ ተሰማ እንዳሉት አለም  ወደ አንድ መንደር እየመጣች ባለበት በአሁኑ ወቅት መከፋፈሉ እና ውጣልኝ መባባሉ ትክክለኛ አካሄድ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ሃገር የምትለወጠው ሁሉም ዜጋ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ዘርፉ የራሱን አሻራ ሲያሳርፍ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ አክቲቪስቶች የሚያስተላልፉት መልእክት ቀና ሊሆን ይገባዋል፤ዜጎችም በስሜት መነዳትን ገትተው መክንያታዊ መሆን እንዳለባቸው ነው መምህሩ የገለጹት፡፡ ስለ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ ተማሪዎች እንደሚማሩ ሁሉ ሌላውም ዜጋ እንዲያውቅ መንግስት ሊሰራ እንደሚገባውም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ እንደ ዜጋ ሰላምን ለማስፈን የተሳሳተውን መንገድ መከተል ሳይሆን በአርአያነት ሌሎችን ወደ ቀና መንገድ መመለስ ይገባል ያሉት መምህሩ በሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ግጭትን የሚያባብሱ ሃይሎች ከህዝብ  የተሰወሩ ባለመሆናቸው ህዝቡ ሊያጋልጣቸው እንደሚገባ  ተናግረዋል፡፡ ”ኢትዮጵያውን በደም የተሳስርን ህዝቦች ሆነን እያለን የአመለካከት አንድነት ባለመፍጠር ወደ ግጭት ማምራታችን ተገቢ አይደለም” ያሉት መምህሩ ፖለቲከኞች የሃገሪቱ ዋነኛ ችግር ድህነትና የቴክኖሎጂ ጥማት መሆኑን ተረድተው እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን ዜጋን ለማፍራት ወጣቶች ምርታማ የሚሆኑበትንና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ማስፈን  ከመንግስት የሚጠበቅ ጉዳይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በሃገራችን ልዩነትን በመንተራስ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና መፈናቀሎች የደካማነት መገለጫና  ከማህበረሰብ እውቀትና ስነምግባርም የሚፃረሩ ናቸው ያሉት ደግሞ መምህር ገበያው ያሳር ናቸው ፡፡ ለግጭት የማይተባበርና ሰላማዊ ዜጋን መፍጠር ከቤተሰብ ይጀምራል ያሉት መምህሩ የጥላቻ ስብከትን  ከየቤታችን ማቆም አለብን ብለዋል፡፡ የሃገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ ከአባቶች የተወረሱት አብሮ የመኖርና የመስራት ፣ጠላትን በጋራ  የመመከት በጎ እሴቶችን ልናዳብራቸው እንጂ ልዩነት መንስኤ ሆኖ ሊያጋጭ እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ህዝባዊ የምክክር መድረኮችን እስከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል በማውረድ ማካሄድ እንደሚገባም  መምህሩ አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም