ዋልያዎቹ አራተኛ የምድብ ጨዋታቸውን ነገ ከኬኒያ ጋር ያደርጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ዋልያዎቹ አራተኛ የምድብ ጨዋታቸውን ነገ ከኬኒያ ጋር ያደርጋሉ
አዲስ አበባ ጥቅምት 3/2011 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጪው የአውሮፓ ዓመት በካሜሮን አዘጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን ነገ ከኬንያ ጋር ያካሄዳል። በአሰልጣኝ አብረሃም መብራቱ የሚመሩት ቡድኑ ጨዋታው ወደሚካሄድበት ኬንያ ባለፈው ሀሙስ አቅንቷል። ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸውም ተገልጿል። ከሦስት ቀን በፊት ሦስተኛ የምድብ ጨዋታቸውን በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዮም ያደረጉት ዋልያዎቹ ከኬኒያ ጋር ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት መለያየታቸው ይታወቃል። ዋልያዎቹ ከዚህ በፊት ባደረጓቸው ጨዋታዎች በጋና 5 ለ 0 ሲሸነፉ ሴራሊዮንን ደግሞ 1 ለ 0 አሸንፈዋል። ይሁን እንጂ የሴራሊዮን መንግስት በአፍሪካ እግር ኳስን እየመሩ ካሉ ፕሬዚዳንቶች ብቸኛው እንስት የነበሩትን ኢሻ ጆንሰንና የጽህፈት ቤት ኃላፊው ክርስቶፎር ካማራን ከሙስና ጋር በተያያዝ ከስራ አሰናብቷል። ከስራ የተሰናበቱት የሴራሊዮን የእግር ኳስ አመራሮች አላግባብ ከስራ ተሰናብተናል በሚል ለፊፋ ባቀረቡት ቅሬታ መሰረት የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር /ፊፋ/ የሴራሊዮን መንግስት በእግር ኳሱ ጣልቃ ገብቷል በሚል የሴራሊዮን የእግር ኳስን ከዓለም አቀፍ ውድድር ለጊዜው አግዷል። ሴራሊዮን በዓለምና አህጉር አቀፍ ደረጃ ከውድድር መታዷን ተከትሎ ከትናንት በስቲያ ከጋና ጋር በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የነበራት ጨዋታ ተሰርዟል። ፊፋ በሴራሊዮን ላይ የጣለው ጊዜያዊ እገዳ ፀንቶ አገሪቱ ከአፍሪካ ዋንጫ የምትወጣ ከሆን ዋልያዎቹ ሴራሊዮንን በማሸነፍ ያገኙት ሦስት ነጥብ ሊሰረዝ ይችላል። አሁን ባለው ውጤት ግን ዋልያዎቹ በተደለደሉበት ምድብ ስድስት፤ ኬንያ ሦስት ጨዋታዎችን አድርገው በአራት ነጥብ እመራች ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደግሞ አራት ነጥብ ቢኖረውም በጎል ክፍያ ተበልጦ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ጋና እና ሴራሊዮን ደግሞ እያንዳንዳቸው ሁለት ጨዋታዎችን አድርገው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።