ቀጥታ፡

አየር መንገዱ የቦይንግ 787 ጅንኤክስ የሞተር ጥገና አገልግሎት መስጠት ጀመረ

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ብቸኛ የሆነውን የቦይንግ 787 ጅንኤክስ የሞተር ጥገና አገልግሎት በአገር ውስጥ መስጠት ጀመረ። አየር መንገዱ የቦይንግ 787 ድሪም ላይነር አውሮፕላን ተረክቦ ሥራ ከጀመረ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም የአውሮፕላኖቹን ሞተር ጥገና የሚያካሄደው ወደውጭ አገራት በመላክ ነበር። አሁን ግን ጥገናውን በአገር ውስጥ ለማከናወን የሚያስችለውን አቅም ፈጥሯል፤ በመሆኑም የጥገና አገልግሎቱን በራሱ ለማከናወን የሚያስችለውን ማእከል ዛሬ በይፋ አስመርቋል። በዚህም አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም ለአውሮፕላኖች ጥገና ያወጣ የነበረውን በሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ወጪ ማዳን የሚችል ከመሆኑም በላይ ወደፊት የሌሎች አየር መንገድ አውሮፕላኖችን መሰል ሞተሮች በመጠገን ገቢውን ለማጠናከር ያስችለዋል ተብሏል። የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ በቴክኖሎጂ ወደር የማይገኝለት የቦይንግ 787 ጅንኤክስ የሞተር ጥገና አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ጠቀሜታው "ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካም የሚተርፍ ነው" ብለዋል። በተጨማሪም ይህንን አቅም በመጠቀም የሌሎች አየር መንገዶችን አውሮፕላን ሞተሮች በመጠገን ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እንደሚረዳ የተናገሩት አቶ ተወልደ ይህም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ነው የገለፁት። አየር መንገዱ ከ100 በላይ በሆኑ አውሮፕላኖች የበረራ አገልግሎት መስጠት በመጀመር ከአፍሪካ ቀዳሚው አየር መንገድ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1962 በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የጀት ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የጀመረ አየር መንገድ ነው። በተጨማሪም አየር መንገዱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2012 ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን እንዲሁም በ2016 ኤር ባስ ኤ350 ደብሊው ኤክስ ቢ አውሮፕላንን በመግዛትና በመጠቀም በአፍሪካ የመጀመሪያው አየር መንገድ እንደሆነም ይታወቃል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም