በአመራሮች የሚስተዋለው ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ችግር ሊፈታ ይገባል...የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት - ኢዜአ አማርኛ
በአመራሮች የሚስተዋለው ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ችግር ሊፈታ ይገባል...የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት
ሐረር ጥቅምት 2/2011 በሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች የሚስተዋለው ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ችግር ሊስተካከል ይገባል ሲሉ አባላቱ ጠየቁ። የኮሚሽኑ የጸጥታ አባላት በኮሚሽኑ አሰራርና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙራድ አብዱላሃዲና ከደቡብ ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል በላይ ስዩም ጋር ተወያይተዋል። አባላቱ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት የኮሚሽኑ አመራሮች ከሥራ ይልቅ ለግል ጥቅም ቅድሚያ እንደሚሰጡና ቡድናዊነት ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ከተሳታፊዎች መካከል ምክትል ሳጅን አላዛር አዳም እንደተናገሩት በኮሚሽኑ አመራሮች ላይ ቡድናዊ ሥራ መጎልበት፣ይህን መሰረት አድርጎ መመደብና ሌሎችም አግባብ ያልሆኑ ስራዎች በስራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። "በአመራሩ የሚስተዋለው የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈታ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ብንጠይቅም ምላሽ አጥተናል፣ ሥራችንን በአግባቡ ብናከናውንም ለጥያቄያችን መፍትሄ እንሻለን" ብለዋል። "የኮሚሽኑ አመራሮች በኪራይ ሰብሳቢነትና በኮንትሮባንድ ሥራዎች ተዘፍቀው እየታዩ ምንም የእርምት እርምጃ ሲወሰድ አላየንም " ያለው ደግሞ ምክትል ሳጅን ኢስማኢል አህመድ ነው። "አንድ ተራ አባል ቀላል ጥፋት ሲያጠፋ በህግ ይጠየቃል፤ በአመራሩ ላይ ለሚስተዋለው ብለሹ አሰራር ግን መፍትሄ ሲወሰድ አይታይም፤ ይህ አሰራር ቅሬታ እየፈጠረብን ስለሆነ የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል ሲል" ጠይቋል። ዋና ሳጅን አንዋር መሀመድ በበኩላቸው " የፖሊስ አባላቱ የምንጠይቀውን የጥቅማ ጥቅምና አሉ የሚባሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍታት ይገባል፤ ቡድናዊና ብልሹ አሰራሮችም መፈተሽ አለባቸው" ብለዋል። እርሳቸውን ጨምሮ የፖሊስ አባላቱ የሚጠበቅባቸውን ህዝባዊ አገልግሎት በተሻለ ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑ መናገራቸውም ተደምጧል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል በላይ ስዩም የክልሉ ፖሊስ አባላት የህግ የበላይነትንና የክልሉን ጸጥታ በማስከበር በኩል ከተለያዩ አካላት ጋር ተባብሮ ይሰራ እንደነበር አስታውሰዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አባላቱ ካሏቸው የመልካም አስተዳደርና መሰል ጥያቄዎች የተነሳ ህዝብን በኃላፊነት ስሜት የማገልገል ሥራቸው እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ጠቁመዋል። "ይህም በህብረተሰቡ ላይ የጸጥታ ስጋት እያሳደረ ይገኛል" ያሉት ሜጀር ጄነራል በላይ፣ በአመራሮች የተለያዩ አድሎዓዊ አሰራር ቢፈጸም እንኳ ስራን በአግባቡ በማከናወን መብታቸውን መጠየቅ እንዳለባቸው አስረድተዋል። ችግሮችን ተቀራርቦ በመነጋገር በውይይት መፍታት ተገቢ መሆኑንም ነው ያመለከቱት። አባላቱ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ነጻ በመሆን የህብረተሰቡን ሰላምና ጸጥታ ማስከበር ኃላፊነትን መወጣት ቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑን ገልጸው ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት ልምዳቸውንም ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙራድ አብዱልሃዲ በበኩላቸው አባላቱ ለችግሩ ተጠያቂው አመራሩ መሆኑና ይህን በማረም በኩል የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል። "ቡድን በመመስረትና በተለያየ መንገድ በአባላቱ መካከል መከፋፈልን ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አመራሮችን በመለየት ተገቢ የእርምት እርምጃ ይወሰዳል" ሲሉም ተደምጠዋል። ችግሮቹ በሂደት የሚፈቱ መሆኑን አባላቱ ተገንዝበው የተጣለባቸው ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንድሚገባ አሳስበዋል። በጨልንቆ ሰማዕታት መሰብሰቢያ አዳራሽ ትናንት በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የክልሉ መደበኛ ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል፣ ትራፊክ እና የእሳት አደጋ መከላከል አባላት ተገኝተዋል