ቀጥታ፡

ለኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት የተሰጠው ትኩረት በድንበር አካባቢዎች ለሚኖሩ ህዝቦች እፎይታ ይሰጣል-የሰቲት ሁመራ ነዋሪዎች

ሁመራ ጥቅምት 2/2011 መንግሥት በዚህ ዓመት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎቹ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነትን እንደሚያጠናክር መግለጹ በድንበር አካባቢዎች ለሚኖሩ ህዝቦች እፎይታ እንደሰጠ በትግራይ ምዕራባዊ ዞን የሰቲት ሁመራ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ ነዋሪዎቹ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ  በዓመቱ የመንግሥት አቅጣጫዎች ላይ የኢትዮ- ኤርትራ ዘላቂ ሰላምን  ለማስቀጠልና የድንበር ንግድ ጉዳዮችን ማካተታቸው ደስታ እንደፈጠረባቸው ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡ አቶ ዑቅባይ አማረ የተባሉት ነዋሪ መንግሥት በ2011 የትኩረት አቅጣጫዎቹ ውስጥ ለሁለቱ አገሮች ግንኙነት መጠናከር እንደሚሰራ መግለጹ በአዋሳኝ አካባቢዎች ለሚኖሩት መረጋጋትን ይፈጥራል ብለዋል፡፡ በተለይም  አሁን የተጀመረው የድንበር ንግድ በሥርዓትና በህግ እንዲመራ እንደሚሰራ ፕሬዝዳንቱ መናገራቸው በድንበር ላይ የሚኖሩ ህዘቦችን ተጠቃሚ ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው በመንግሥት ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች የኮንትሮባንድ ንግድን ማስቀረትና የድንበር ንግድን በመጀመር በአዋሳኝ አካባቢዎች ያሉትን  ህዝቦች ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ተመስገን ገብረ መድኅን ናቸው፡፡ መንግሥት ለሰላምና ለህግ በላይነት መረጋገጥ፣ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠልና የኢትዮጵያውያን አብሮነት ለማጠናከር ትኩረት መሰጠቱን  በህዝቡ ዘንድ ተስፋ ማሳደሩንም ይገልጻሉ፡፡ በቃፍታ ሁመራ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ አቶ መሐመድ ብርሃን ያሲን እንደገለጹት በኢንቨስትመንትና በንግድ ጉዳዮች የሚደረግ ቁጥጥርና ማሻሻያ አገሪቱንም ሆነ ባለሃብቱን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አብረሃት ሓድጉ  መንግሥት ለዓመቱ የያዘው ዕቅድ  በአገሪቱ ሰላም፣ መግባባትና አንድነት ያመጣል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ  ያስቀመጧቸውን የመንግሥት አቅጣጫዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የሕዝብ ተወካየዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት ለህዝባቸውና ለአገራቸው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም