ቀጥታ፡

አገራዊውን የመድኃኒት ፍላጎትና አቅርቦትን 95 በመቶ ለማጣጣም የሚያስችል ግዢ እየተካሄደ ነው፡፡

አዳማ  ጥቅምት 2/2011 አገራዊው የመድኃኒት ፍላጎትና አቅርቦቱን 95 በመቶ የሚያጣጥም ግዢ እየተካሄደ መሆኑን የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ አስታወቀ። ከ11 የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተወጣጡ ጋዜጠኞች የተሳተፉበት የሚዲያ ፎረም የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡ የኤጀንሲው የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ክምችትና ስርጭት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር  አቶ ተስፋዓለም አድራሮ ለኢዜአ እንደገለጹት ከ10 ዓመታት በፊት የአገሪቱ የመድኃኒት በጀት ከግማሽ ቢሊዮን ብር የዘለለ አልነበረም። የመድኃኒት ፍላጎትና የሚመደበው በጀትም በየዓመቱ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፣ ባለፈው ዓመት ቀደም ብሎ የተገዛ መድኃኒትን ጨምሮ በድምሩ በ16 ቢሊዮን ብር መድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ግዢ ተከናውኗል ብለዋል። አሁን ያለው የመድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች  አቅርቦት ከፍላጎቱ 70 በመቶውን  ብቻ የሚያሟላ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ፣ ይህንን ወደ 95 በመቶ ለማሳደግ በተያዘው ዓመት የ12 ቢሊዮን ብር ግዢ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኤጀንሲው በመላው አገሪቱ የሚገኙ 19 ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችን በክላስተር በማደራጀትና ለጤና ተቋማት አስፈላጊውን የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎችን በወቅቱ በማቅረብ ኅብረተሰቡን ተደራሽ ለማድረግ  ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የኤጀንሲው የህዝብ ግንኝነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አድና በሬ እንደገለፁት የመድኃኒት አቅርቦቱን ከማሟላት ጎን ለጎን ለኅብረተሰቡ በቂ የመድኃኒት መረጃ ለማቅረብ እንዲቻል ሁሉንም የመገናኛ ብዙኃን ያካተተ የሚዲያ ፎረም ተቋቁሞ በትብብር  እየተሰራ ነው። የፎረሙ አባላቱ በዓመት ሁለት ጊዜ እየተገናኙ የኤጀንሲው ዕቅድ ፣ክንውን፣ ያጋጠሙትን ችግሮችና የተሰጡ መፍትሄዎችንና ባልተፈቱ ችግሮች ላይ በመምከር በኤጀንሲው ላይ ግልፀኝነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን አጋዥ ሚና በመጫወት ላይ መሆናቸውን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። ከሚዲያ ተቋማቱ የተወጣጡት ጋዜጠኞች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ላለፉት ሁለት ቀናት በአዳማ ከተማ የተካሄደ ሲሆን፣ ጋዜጠኞቹ በኤጀንሲው የአዳማ ቅርንጫፍ የሥራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል ። በኤጀንሲው የአዳማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ንጉሴ ቅርንጫፉ በኦሮሚያ፣ በአፋርና በአማራ ክልል ለሚገኝ 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ህዝብ የሚያገለግል መድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን እንደሚያከፋፍል ገልጸዋል። በተጠናቀቀው ዓመት እንድ ቢሊዮን ብር የሚገመት መድኃኒት አሰራጭቷል።በዚሀም 29 ሆስፒታሎችና 313 ጤና ጣቢያዎች በአገልግሎቱ ተጠቅመዋል። የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ባልደረባ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ በሰጠችው አስተያየት ኤጀንሲው አሰራሩን ለመገናኛ ብዙኃን በየጊዜው ግልፅ ማድረጉ ኅብረተሰቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲይዝ ይረዳዋል ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኛ ፈቃዱ ከተማ በበኩሉ መድረኩ መድኃኒትን አስመልክቶ ከኅብረተሰቡ ለሚነሱ ቅሬታዎች የተሟላ መረጃ በማግኘት ግልፀኝነት እንዲፈጠርና እውነታውን የሚታወቅበት መረጃ ለማድረስ ያስችላል ብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም