በመቀሌ ከተማ በ147 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካ ምርት ማከፋፈል ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በመቀሌ ከተማ በ147 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካ ምርት ማከፋፈል ጀመረ
መቀሌ ጥቅምት 2/2011 በመቀሌ ከተማ በ147 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ገመድ ተሸካሚ የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካ ምርት ማከፋፈል መጀመሩን አስታወቀ፡፡ "ሙሉ ብርሃን ኢንዱስቱሪና ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር" በሚል የተቋቋመው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ እስራኤል ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለጹት ፋብሪካው በአገር አቀፍ ደራጃ ያለውን የኮንክሪት ምሶሶ ችግር ለመፍታት ታሳቢ ተደርጎ የተቋቋመ ነው፡፡ ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በቀን እስከ 90 የሚደርስ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ተሸካሚ ምሶሶዎችን በማምረት ላይ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር በቀን እስከ 300 የተለያዩ ደረጃ ያላቸው ምሶሶዎችን የማምረት አቅም እንደሚኖረው ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመነጋገር ፋብሪካው ምርቶቹን ለትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች ማከፋፈል መጀመሩን አቶ እስራኤል አስታውቀዋል፡፡ ፋብሪካው ከአገር ውስጥ ስሚንቶ፣ አሸዋና ጠጠር የሚጠቀም ሲሆን ለምሶሶው መሰሪያ የሚውሉ ብረቶችን ከውጭ በማስገባት ለአገልግሎት ያውላል፡፡ ፋብሪካው በሚያመርተው ምርት መንግስት በከተማና በገጠር የኤሌክትሪክ ሽፋን ለማዳረስ እያከናወነ ላለው ስራ አጋዥ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግስት በቦታ አቅርቦትና ብድር በማመቻቸት እገዛ እንዳደረገላቸው የገለጹት አቶ እስራኤል ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት እንዲችል ከውጭ ለሚመጡ ጥሬ ዕቃዎች መግዣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የትግራይ ቅርንጫፍ ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ገብረመድህን የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካው አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ምርቶች ማምረት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካው በመቀሌ ማምረት መጀመሩ ከአሁን ቀደም ከአዲስ አበባ ለማጓጓዝ ለትራንስፖርት ይወጣ የነበረውን ወጪ ይቀንሳል ብለዋል፡፡ ከፍትኛ የኤሌክትሪክ ምሶሶዎች ለ20 አመታት ዋስትና ያላቸው መሆኑን የገለጹት ስራ አስፈፃሚው ካሁን በፊት ለአገልግሎት ይውሉ የነበሩ የባህርዛፍ ምሶሶዎች በጉዳት ምክንያት ያደርሱ የነበሩትን አደጋና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ የሚቀንስ ነው፡፡ የትግራይ ክልል ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃፍቶም ፋንታሁን እንደገለጹት የምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካው በመቀሌ ከተማ ለተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ቦታ ከተሰጣቸው ባለሀብቶች መካከል በፍጥነት ወደ ማምረት ስራ መሸጋገር መቻሉ በአርያነቱ እንዲቀመጥ የሚያደርገው ነው፡፡ የትግራይ ክልል የተረጋጋ ሰላም ያለው በመሆኑ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን የጽህፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በመካኒካል ምህንድስና የተመረቀው ወጣት አማኑኤል ሀይሉ በፋብሪካው በመቀጠር በወር 6ሺህ ብር የወር ደሞዝ እየተከፈለው ይሰራል፡፡ በፋብሪካው የስራ እድል በማግኘቱ ደስተኛ መሆኑን የሚናገረው ወጣት አማኑኤል ገቢ ማግኘት መጀመሩ ከቤተሰብ ጥገኝነት ወጥቶ የራሱን ቤተሰብ ለመመስረት መቻሉን ገልጿል፡፡ ወጣት ዝፉን ኪዳኑ በበኩሏ "ማህበሩ በዘርፉ ኢንቨስት በማድረጉ የአካባቢውን ወጣቶች የሥራ አድል ተጠቃሚ አድርጎናል" ብላለች፡፡ በትግራይ ክልል በ2010 ዓ.ም 24 ቢልዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 1ሺህ 328 ባለሀብቶች በስራ እንዳሉ ከክልሉ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመልክታል፡፡