ቀጥታ፡

የቀድሞ የብሄራዊ ቡድን ተጫዎችና አስልጣኝ ስዩም አባተ የቀብር ስነ-ስርዓት ተፈጸመ

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2011 የቀድሞ  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዎችና አሰልጣኝ ስዩም አባተ የቀብር ስነ-ስርዓት ዛሬ በአዲስ አበባ ሳሪስ በሚገኘው የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ተፈጸመ። አሰልጣኝ ስዩም አባተ በተጫዋችነት ዘመናቸው በቅዱስ ጊዮርጊስና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ወርቃማ ጊዜን አሳልፈዋል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ  ላይ ስኬታማ ከሚባሉ አሰልጣኞች መካከል አንዱ የነበሩት አሰልጣኝ ስዩም አባተ ከ1989 ጀምሮ  በተለያየ ጊዜ የኢትዮጵያ ታዳጊና ወጣት ብሔራዊ ቡድንን፣ ዋናውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የኦሊምፒክ ቡድን አሰልጥነዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ቆርኪና ጣሳ እንደዚሁም ብሔራዊ ትምባሆን ካሰለጠኗቸው የአገሪቱ የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል ይጠቀሳሉ። ኢትዮጵያ ቡናን ጨምሮ በተለያዩ ክለቦች ውስጥም በቴክኒክ ዳይሬክተሪነት አገልግለዋል። አሰልጠኝ ስዩም ከአባታቸው ከአቶ አባተ በቀለና ከእናታቸው ወይዘሮ ማሚቴ ገብረስላሴ በሚያዝያ ወር 1943 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ፍል ውሃ በሚባለው ሰፈር ነበር የተወለዱት፡፡ አሰልጣኝ ስዩሜ ባለትዳርና የሶስት ወንድና ሶስት ሴት ልጆች አባት ነበሩ። አሰልጣኙ በህመም ምክንያት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ህክምናቸውን  ሲከታተሉ ቆይተው በተወለዱ በ68 ዓመታቸው በትናንትናው እለት  ነበር ህይወታቸው ያለፈው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም