የመዲናዋ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች እልባት አላገኙም

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2010 በዋና ዋና የመዲናዋ ጎዳናዎች የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች የእግረኛና የተሽከርካሪ ፍሰትን እያስተጓጎለ ነው፡፡ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ቁጥርና የሁለንተናዊ ዕድገቷን ተከትሎ የሚፈጠር ማህበራዊ ቀውስ በህገ-ወጥ ተግባራት እንቅስቃሴዎች እንድትታጀብ ያደረጋት ይመስላል። የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት “በ2012 ዓ.ም ተደራሽነት ያለው ሕግ በማውጣትና በማስተግበር ተምሳሌት ከሆኑ 10 የዓለም የከተማ ምክር ቤቶች አንዱ መሆን” የሚል ራዕይ ሰንቋል። በከተማ አስተዳደሩ የሚወጡ ሕግና ደንቦችን ለማስከበርም በአዋጅ የደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽህፈት ቤት ቢቋቋምም ሕገ-ወጥ የከተማ እንቅስቃሴዎች እልባት ያገኙ አይመስልም። በርካቶችም ከተማዋ ያወጣቻቸውን ሕግና ደንቦች እያስከበረች አይደለም፤ የመዲናዋ ነዋሪዎችም ሆነ በከተማዋ የተረጋጋ ምጣኔ ሀብት ላይ ተዕጽኖ እያሳደረ ነው በማለት የደንብ አስከባሪው ተቋም ላይ ትችት ይሰነዘራሉ። በዋና ዋና የመዲናዋ ጎዳናዎች የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች የእግረኛና የተሽከርካሪ ፍሰትን ሲያስተጓጉሉ ይስተዋላል። የከተማዋ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ኮማንደር አሳዬ አምባዬ እንደሚሉት ተቋሙ "አቅም በፈቀደው መጠን እየሰራ ነው፤ ህገ ወጥነቱም ከከተማዋ ዕድገት ጋር እየተበራከተ ነው"። "ህገ-ወጥነትን ማስወገድ ዘበት ነው ፤ስርዓት ማስያዝ እንጂ" የሚሉት ስራ አስኪያጁ፤ ጽህፈት ቤቱ ጤናማና የተረጋጋ ንግድ እንዲሰፍን የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን ይገልጻሉ። ደንብ በማስከበር ሂደቱ በአባላቱ ላይ የማስፈራራትና የመደለል ተግባራት እንደሚስተዋሉም አልሸሸጉም። በከተማዋ የሚስተዋለው የህገ-ወጥነት መበራከትን ተከትሎም ተቋማቸው ጽዱ፣ ውብ፣ የተረጋጋች ከተማ እንድትሆን የአደረጃጅትና የግብዓት አቅሙን እያሳደገ እንደሆነ ያብራራሉ። ጽህፈት ቤቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከከተማዋ የህግ ጥሰቶች ላይ በተወሰደ የቅጣት እርምጃ ከ16 ሚሊዮን ብር ለከተማ አስተዳደሩ ገቢ ማድረጉን አስታውቋል። በተለይም ከሕገ-ወጥ መሬት ወረራ፣ ህገ-ወጥ ንግድ፣ ህገ-ወጥ ግንባታ፣ በሀሺሽና ሱስ፣ የግንባታ ተረፈ ምርቶችና ሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራት የተሰበሰበ እንደሆነ አመልክተዋል። ሕገ-ወጥ ተግባራትን በቅጣት ብቻ መከላከል እንደማይቻል ገልጸው፤ ከቅጣቱ ጎን ለጎን የግንዛቤ ትምህርት በመስጠትም ከድርጊቱ እንዲታቀቡ የማድረግ ስራዎች መከናወናቸውን አውስተዋል። “ህገ-ወጥ ከሆነ ደንብ መጣ የሚል አስተሳስብ ተፈጥሯል” የሚሉት ኮማንደር አሳዬ፤ ይህን አስተሳስብ ለመቅረፍ መገናኛ ብዙሃንም ሆነ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም