የትምህርትና ሥልጠናው ፍኖተ ካርታ የጥራት ችግርን እንደሚያቃልል የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርትና ሥልጠናው ፍኖተ ካርታ የጥራት ችግርን እንደሚያቃልል የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ገለጸ
ጎባ/ነቀምቴ ጥቅምት 2/2011 የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ችግሮች እንደሚያቃልል የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ገለጸ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለፍኖተ ካርታ ግብዓቶች ለማሰባሰብ የምክክር መድረክ ለሁለት ቀናት አካሂዷል፡፡ ማህበረሰቡ ፍኖተ-ካርታው ምሁራንና ባለድርሻ አካላት የሚሰጧቸውን ምክረ ሀሳቦችን በማከልና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገቡ ጭብጦችን በመያዝ ለተግባራዊነቱ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል። የዩኒቨርሲቲው የሥነ -ትምህርትና ሥነ -ባህሪ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አሸብር ደመቃ ፍኖተ- ካርታ አሁን እየተሰራበት ባለው የትምህርት ፖሊሲ ላይ የሚነሱ የትምህርት ጥራትና አደረጃጀት ችግሮችን በዝርዝር የፈተሸና ዘላቂ መፍትሄ በሚያመጣ መልኩ የተቀረፀ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብለዋል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች በአፍ መፍቻቸውና በሌሎች አራት የሚሆኑ ቋንቋዎችን በአንዴ እንዲሰለጥኑ የቀረበው ሀሳብ ግን ሊጤን እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የቤተ መጻህፍትና ቤተ መዛግብት ክፍል ባልደረባ አቶ መኮንን ጉደታ በበኩላቸው “በፍኖተ ካርታው አሁን እየተሰራበት ባለው የትምህርት ፖሊሲ በዋነኛነት የሚስተዋሉ የግብረ ገብነትና የተግባር ተኮር ትምህርት ክፍተቶችን በመለየት ማስተካከልና ወደ ውጤታማነት መቀየር የሚያስችል አቅጣጫ መቀመጡ ውጤታማ ያደርገዋል” ብለዋል፡፡ ተማሪዎች በክህሎት የዳበሩና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፎች ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ በመደበኛ የትምህርት ዘርፍ መሰጠት እንዳለባቸው በፍኖተ ካርታው መካተቱም ለሥራ ፈጠራ ጥበብ የተሰጠውን ትኩረት እንደሚያሳይ ገልጸዋል። በበቂ ቤተ- ሙከራና የሰው ኃይል ያልተደራጁ የከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ፍኖተ ካርታውን ለመተግበር እንቅፋት እንዳይሆኑ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ የትምህርት ክፍል መምህር አቶ ኪሩቤል አማረ በበኩላቸው ካርታ ይዟቸው የመጡት ማሻሻያዎች የሚያበረታቱ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ ፍኖተ ካርታውን ለመተግበር የሀብት ምንጮች በማፈላለግና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በመፍትሄነት የተያዙ አማራጮችን ማካተት ነበረበት ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ማህበረሰባዊ አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ስሜነህ ቤሴ በበኩላቸው ፍኖተ-ካርታው ጥልቅ ጥናት የተደረገበት፣ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የተነሳና የአደረጃጀት ግልጽነት ችግር የሌለበት ነው ይሉታል፡፡ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች በፍኖተ ካርታው ሊዳብሩ ይገባቸዋል ባሏቸው ሀሳቦች ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል ፡፡ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ከ14ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችና በቅድመና ድህረ ምረቃ መርሐ ግብር ተቀብሎ በማስተማር ላይ ነው፡፡ በተያያዘ ዜና ረቂቅ የትምህርት ፍኖተ ካርታው በአገሪቱ እየታየ ላለው የትምህርት ጥራት በመፍታት ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናግረዋል። ምሁራኑ በውይይቱ ላይ ፍኖተ ካርታው እየወደቀ ያለውን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡ በተለይ በቋንቋ አጠቃቀምና በመምህራን አመዳደብ ዙሪያ የሚታዩትን ክፍተቶች ከመፍታት አኳያ ድርሻቸውን እንወጣለን ብለዋል፡፡