ቀጥታ፡

በአገሪቱ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ኤሌክትሪክ ኃይል ማዕከላት ግንባታ እያካሄደች መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታወቀ

ማይጨው ጥቅምት 2/2011 ኢትዮጵያ ለጀመረችው የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተግባራዊነት በፀሐይ የሚሰሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ማዕከላት ግንባታ እያካሄደች  መሆኑን የውሃ፣መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ። በዘርፉን ከተሰማሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል የጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅትና አይሪሽ ኤይድ ይጠቀሳሉ። በትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን ሕንጣሎ ዋጅራት ወረዳ ልዩ ስሙ ‘‘መሳኑ‘‘ በተባለው ገጠር ቀበሌ በሁለቱም የልማት ድርጅቶች የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ የተገነባው የፀሐይ ኃይል ማዕከል የአካባቢው ህዝብ ትናንት ተረክቦታል። በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ የውሃ፣መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ልዩ አማካሪ አቶ አስረስ ወልደ ጊዮርጊስ እንዳሉት፣ኢትዮጰያ የጀመረችው የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስኬታማ ለማድረግ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል። መንግሥት ታዳሽ የኤሌክትሪክ የኃይል ግንባታዎችን እያካሄደ መሆኑንና ከፀሐይ ኃይል ብቻ የመብራት አገልግሎት አቅርቦትን ለማሻሻል 25 ማዕከላት ተገንብተው በገጠር የሚኖር ከ125 ሺህ ህዝብ በላይ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም የጀርመን ዓለም አቀፍ ልማትና አይሪሽ ኤይድ የተባሉት ድርጅቶች ተቀናጅተው ባደረጉት ድጋፍ በትግራይና በደቡብ ክልሎች የትምህርት፣ጤናና የግብርና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ጥራትና ፍጥነት ያለው አገልግሎት ከማዕከላቱ አግኝተዋል ብለዋል። የጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስስ ካርለይ ባንስባሽ እንዳሉት፣ድርጅታቸው ከአይሪሽ ኤይድ ጋር በመተባበር ባለፉት ዓመታት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ወጪ የተገነቡ 25 ማዕከላትን ለአገልግሎት አብቅቷል። ማዕከላቱ በኤሌክትሪክ  አቅርቦት፣በጤና ተቋማት ውስጥ የህክምና አገልግሎት፣በኮምዩተር የታገዘ  የመማር ማስተማር ሥራን በጥራትና በፍጥነት በማቅረብ በሴቶች ላይ የነበረውን የሥራ ጫና መቀነሳቸውን ተናግረዋል። በዚህም ከኢትዮጵያ ድህነትን ለማጥፋት ለምታደርገው ጥረት እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በገጠራማ አካባቢዎች የሚገኘውን ኅብረተሰብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግሎትን ለማሻሻል  ድርጅቶቹ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በአይሪሽ ኤይድ የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ፓትሪክ ማማነስ ናቸው። እያንዳንዳቸው ለአምስት ሺህ  ህዝብ አገልግሎት የሚሰጡትን ማዕከላት በመገንባት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ህዝብ ተጠቃሚ አድርገዋል። በተጨማሪም በአካባቢዎቹ የሚገኙ 71 የጤና፣ የትምህርት፣የገበሬዎች ማሰልጠኛ ማዕከላትና ሌሎች የማህበራዊ መስጫ ተቋማት በጥራትና  በፍጥነት አገልግሎት ለመስጠት እንዳስቻሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ከአካባቢው ነዋሪዎች መካካል የአራት ልጆች እናት የሆኑ አርሶ አደር ታደሉ ደሳለኝ፣በድርጅቶቹ በተገነቡት የሶላር የኤሌክትሪክ መብራት ኃይል ማመንጫ ማዕከላት በመጠቀማቸው ጊዚያቸውን ለእርሻ ሥራቸው ከማዋል ባለፈ፤ የደን ውድመትን መቀነሳቸውን ገልጸዋል። የመሳኑ ቀበሌው ነዋሪው የ75 ዓመቱ አዛውንት አቶ ካሕሳይ ሽሙዬ በበኩላቸው፣ከፀሐይ በሚመነጨውን አማራጭ ኃይል ቴሌቪዠን ለማየትና ሌሎች አገልግሎትን መጠቀም ጀምረናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም