ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ወታደራዊ አቋምና የሠላም ማስከበር ተልዕኮ የሚደነቅ ነው - የኩባ ልዑካን ቡድን

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2011 ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላት ወታደራዊ አቋምና የሠላም ማስከበር ተልዕኮ የሚደነቅ መሆኑን የሰላም ማስከበር የስልጠናና ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያን የጎበኙ የኩባ የልዑካን ቡድን አበላት ገለጹ። በአገሪቱ የጦር ጄኔራል ራሞን ኢስፓኖሳ ማረቲን የተመራው ቡድን የኢትዮጵያን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አስመልክቶ ገለፃ ተደርጎለታል። ኩባ ድጋፏን የሰጠችበትና የ1969 ዓ.ም የሶማሊያ ወረራ ድል የተመታበትን 40ኛ ዓመት ለማክበር የመጡት የልዑካን ቡድኑ አባላት የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ሚና የሚደነቅ መሆኑን መስክረዋል። በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም የተዋጉ ጄኔራሎች መምሪያውን በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት ለምስራቅ አፍሪካ የሰላም ዋልታ የሆነችውን ኢትዮጵያን መደገፋችን ትክክለኛ ውሳኔና የሚያኮራንም ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ እገዛ በምትፈልግበት በማንኛውም መስክ የኩባ መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም ገልፀዋል። ሁለቱ አገራት በአሁኑ ወቅት በትምህርት፣ በጤናና በቴክኖሎጂ ሽግግር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል። የመምሪያው አዛዥ ተጠባባቂ ብርጋዴር ጄኔራል ሀብታሙ ጥላሁን የኩባ መንግስት ለኢትዮጵያ ያደረገው ውለታ የሚዘነጋ አለመሆኑን ለልዑካን ቡድኑ ገለጸዋል። በሶማሊያ ወረራ ወቅት ኩባ ወታደሮቿን አሰማርታ ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟ አገሪቷ ጠንካራ የመከላከያ ተቋም እንዲኖራት በማድረግ ረገድ ድርሻ እንዳለው ገልጸው "ከሂደቱ ብዙ ቁም ነገሮች ተምረንበታል" ብለዋል። የኢትዮጵያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ የደካሞችን ቤት መስራት፣ በድንገተኛ አደጋዎች ወቅት ድጋፍ ማድረግና ሌሎች የማህበረሰብ አገልግሎቶችን እንደሚያጠቃልል ለልዑካን ቡድኑ አባላት ገልጸውላቸዋል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በመንግስታቱ ድርጅት በሚመራው የሰላም አስከባሪ ኃይል በደቡብ ሱዳን አብዬ፣ ዳርፉርና በአፍሪካ ህብረት በሚመራው የሶማሊያ ተልዕኮ ከ12 ሺህ በላይ ወታደሮችን ማሰማራቷንም ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም