የውጭ ኩባንያዎች የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ተሳትፎ እየጨመረ ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ኩባንያዎች የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ተሳትፎ እየጨመረ ነው ተባለ
አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2011 የውጭ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ውስጥ የሚያደርጉት ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ። የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ የምጣኔ ኃብት መዋቅር ላይ ዓይነተኛ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚታሰበውን የኢንዱስትሪ ልማት ለማፋጠን ስትራቴጂ ቀርፆ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። ይህንኑ እውን ማድረግ ይቻል ዘንድም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሰፋፊ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ሥራ ጀምረዋል ፤ ሌሎችም በግንባታ ላይ ናቸው። በክልሎችና በውጭ ኩባንያዎች የተገነቡና የሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ በሁለተኛው የእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅድ ማገባደጃ 2012 ዓ.ም በአጠቃላይ 30 የኢንዱስትሪ ፓርኮች በኢትዮጵያ ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም መሰረት የተለያዩ አገራት ኩባንያዎችም ኮርፖሬሽኑ በሚያለማቸው ፓርኮች ውስጥ ግንባታ መጀመራቸውን ነው በኮርፖሬሽኑ የኦፐሬሽንና ማኔጅመንት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን ለኢዜአ የገለፁት። ኮምቦልቻ፣ መቀሌ፣ ድሬደዋ፣ አዳማና አረርቲ በውጭ ባለሃብቶች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እየተካሄደባቸው ከሚገኙ መካከል ናቸው። በኮምፖልቻ ካርቪኮ የተሰኘ የጣሊያን ኩባንያ እያካሄደ ያለው አልባሳትና ጨርቃጨርቅ ማምረቻ ግንባታ አንዱ ሲሆን ይህም ለኢትዮጵያ በዘርፉ የተሻለ ልምድ ይዞ ይመጣል ተብሏል። በዚሁ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሌላ የቻይና ኩባንያ መሬት ተረክቦ ግንባታ ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም አንስተዋል። በድሬዳዋም እንዲሁ ሊያንፋ የተሰኘ የሞሮኮ ኩባንያ እና ሌሎች ሶስት የቻይና ኩባንያዎችም ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማልማት እየሰሩ ነው ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል። ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር ጋር የተቆራኘውና በምጣኔ ኃብታዊ አዋጭነቱ ከፍተኛ ትኩረትን ይስባል በተባለው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥም አራት ኩባንያዎች ግንባታ ጀምረዋል። ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ መሰረተ ልማት አቅራቢ መንግስታዊ ድርጅቶችን አቀናጅቶ መስራቱ ባለኃብቶቹ እንዲሳቡ ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ይናገራሉ። የፍሳሽ ማጣሪያ አገልግሎት፣ የውሃ አቅርቦትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በፓርኮቹ ውሰጥ እንዲኖሩ መደረጋቸው አልሚዎቹን ለመሳብ ያስቻሉ ሁኔታዎች ናቸው ተብሏል። ይህም ባለሃብቶች ለመሰረተልማት ግንባታ የሚወስድባቸውን ጊዜ እና ወጪ ከመቀነስ ባሻገረ ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ ያስችላቸዋል ሲሉ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በኮምቦልቻ፣ ድሬደዋ፣ መቀሌ እና አዳማ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመንግስት የተገነቡ 43 ያህል የተለያየ መጠን ያላቸው የማምረቻ ሼዶች ወደ ስራ ገብተዋል። በነዚህም በርካታ ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ግኝትንም ያሰፋል ተብሎ ይጠበቃል። በአሁኑ ወቅት ሥራ የጀመሩት ፓርኮች 60 ሺህ የማኑፋክቸሪንግ የስራ ዕድል ፈጥረዋል።