"ጋምቤላ የታደለችውን ጸጋ በአግባቡ በመጠቀም ክልሉንና ኢትዮጵያን የተሻለች ማድረግ ይገባል"- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

17
አዲስ አበባ ግንቦት 13/2010 እምቅ የተፈጥሮ ኃብት ባለቤት የሆነችው ጋምቤላ የታደለችውን ጸጋ በአግባቡ በመጠቀም ክልሉንና ኢትዮጵያን የተሻለች ለማድረግ መስራት እንደሚገባ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋምቤላ ክልል ባደረጉት የሁለተኛ ቀን ጉብኝት በጋምቤላ ስታዲየም በመገኘት ለከተማዋና አካባቢው ነዋሪዎች ንግግር አድርገዋል። በረሀማነትን ከልምላሜ አቀናጅታ ያቀፈችው ጋምቤላ ከህዝቡ የልማት ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ልማት ለማስመዝገብ ልትሰራ ይገባል ነው ያሉት። በንግግራቸው "አገሪቱን ከወራሪዎች ለመከላከል በተደረገ እልህ አስጨራሽ ትግል የጀግኖች ጀግና ተምሳሌት የሆኑት የጋምቤላ የቁርጥ ቀን ልጆች ተጠቃሽ ናቸው" ብለዋል። የአገሪቱ ህዝብ ወኔውን ወደ ልማት ማዞር አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእምቅ የተፈጥሮ ኃብት ባለቤት የሆነችው ጋምቤላ የታደለችውን ጸጋ በአግባቡ በመጠቀም ክልሉንና ኢትዮጵያን የተሻለች ለማድረግ መስራት ይገባል ነው ያሉት። ''ኢትዮጵያዊያን ብዙ ያለንን የማናውቅ የሌለንን በማለም የኖርን ህዝቦች ነን'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱን ከዛሬ የተሻለች ለማድረግ ጠንክሮ መስራት ተገቢ ነው ብለዋል። የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ጋትሉዋክ ቱት "ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመመረጣቸው የጋምቤላ ሀዝብ እጅግ ደስተኛ ነው" በማለት፤ ህዝቡን ማወያየታቸውንም ያደነቁ ሲሆን የጋምቤላ ህዝብ ከጎናቸው ይሆናል ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም